በመሬትና መሬት ነክ ጉዳዮች ላይ በተደረገ ጥናት ዙሪያ ውይይት እየተካሄደ ነው

ግንቦት 21/2014 (ዋልታ) በመሬትና መሬት ነክ ጉዳዮች ላይ የሚስተዋሉ ችግሮች እንዲሁም የመፍትሔ አማራጮችን ለማመላከት በተደረገ ጥናት ላይ ውይይት እየተደረገ ነው።

በውይይቱም በአዲስ አበባ ከተማ የመንግሥትን ሀብት ለማልማት እንቅፋት የሚሆኑ በፍርድ ቤት ጊዜያዊ እግዶች በኩል የሚስተዋሉ ችግሮችን በጋራ መፍታት ይጠይቃል ተብሏል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ መድረኩ ጥናትን መሰረት ያደረገ አካሄድ ለመያዝና ከተማችንን በጋራ ለማልማት ያለመ ነው ብለዋል።

የከተማው ፍትህ ቢሮ ኃላፊ ፅዋዬ ሙሉነህ በበኩላቸው የከተማዋን ሁለንተናዊ ልማት ለማከናወን መጓተት ከሚፈጥሩት ችግሮች መካከል አንዱ የፍርድ ቤቶች ጊዜያዊ ዕቅዶች እንደሆኑ ጠቁመዋል፡፡

በመሆኑም የተቀላጠፈ፣ ፍትሐዊ እና የመንግሥት ሀብትን በአግባቡ ለመጠቀም እንቅፋት የሚሆኑ ችግሮችን ለይቶ ለውይይት ያቀረበ ጥናት እንደሆነ ገልፀዋል።

ውይይቱ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሚከራከርባቸውን የመሬትና መሬት ነክ ጉዳዮች እና የጊዜያዊ እግዶችን በተመለከተ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተጠና ሰነድ ላይ መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ጥናቱ በዘርፉ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮች፣ የመፍትሔ አማራጮችና የትግበራ መመሪያዎችን ማካተቱ ተጠቁሟል።

በመድረኩ ላይ የፍትህ ሚኒስቴር የሥራ ኃላፊዎች፣ የፍርድ ቤቶች ዳኞች፣ የተወካዮች ምክር  ቤት ቋሚ ኮሚቴ አባላት፣ አቃቤ ሕጎችና ሌሎች የፌዴራልና የክልል የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።