በነጻ ቃጠሎ የሚያክመው ዶክተር



ሮጣ ላልጠገበች፣ የነገ ጮራን አሻግራ ለማየት ለምትታትር ሕጻን ከሕሙማን አልጋ ላይ መዋል አስከፊ የሕይወት ገጽታ ነው። የልጅ ሲቃ የወላጅን ቅስም ይሰብራል።

ወላጆች ከሕጻናት ጋር በምትጫወትበት ወቅት በልጃቸው ላይ የእሳት አደጋ እንደደረሰባት ይናገራሉ። በህጻኗ እግር ላይ የደረሰው የእሳት አደጋ እግሯ ይቆረጣል እስከመባል አደረሳት።

በዚህም በልጃቸው ዳግም የመራመድ እድል ላይ ተስፋ የቆረጡት ወላጆች ለዓመታት ቢቆዩም በኖርያዊው ዶክተር አይነር ኤሪክሰን ተስፋቸው ዳግም ተመልሷል። ወላጆች በልጃቸው ላይ በተደረገው ሕክምና አሁን ተስፋቸው ቀጥሏል። ሐኪሞቹ ተገቢውን ሕክምና ከመስጠት ባለፈ እንደ ልጆቻቸው የእሳት አደጋ የደረሰባትን ህጻን ተንከባክበው ለዚህ አስገራሚ ለውጥ በማድረሳቸው አሁን የወላጆች ደስታ ወደር የለውም።

በዘርፉ አስፈላጊውን የሕክምና ትምህርት ተምረው ወደ ኢትዮጵያ አርባ ምንጭ ከተማ በመመለስ ብዙዎችን ያከሙ፣ የብዙዎችን ነገ ብሩህ ያደረጉ፣ የበርካቶችን ተስፋ የመለሱ ሰው ናቸው ዶክተር አይነር ኤሪክሰን።

ዶክተር አይነር ኤሪክሰን መጀመሪያ ወደ ይርጋ አለም ሆስፒታል ስመጣ እንደማንኛውም ሀኪም የህክምና እርዳታ ለመስጠት ነበር፤ ከዚያ ግን አንድ ነገር ቀልቤን ሰረቀው ይሄውም በተለያዬ አደጋ ሰውነታቸው ተቃጥሎ የሚመጡ ታካሚዎች ናቸው ይላሉ።

“እነዚህ ታካሚዎች ወደ ሆስፒታል ሲመጡ ዓለም በደረሰበት ቴክኖሎጂ ሕክምናን አያገኙም ነበር፤ ታካሚዎች ሲሰቃዩ ማየት ልብ ይሰብራል፤ ሕክምናው ሲሰጣቸው በረድ የሚልላቸውን ስቃይ መመልከቴ ደግሞ ለራሴ አንድ ነገር ቃል እንድገባ አድርጎኛል” ሲሉም ይገልጻሉ።

እስካሁን በሰጡት የእሳት አደጋ ቃጠሎ ሕክምና በአደጋ የተጣመመ እጅን አቃንተዋል፣ በእሳት አደጋ ምክንያት አንገታቸው እና ደረታቸው ተጣብቆ የነበሩ ግለሰቦችን በዘመነ የሕክምና ጥበብ ወደ ቀደመ አቋማቸው መመለስ ችለዋል።

ዶክተር አይነር ኤሪክሰን የእሳት አደጋ የሕክምና ማዕከል አቋቁመዋል። ሕክምናውን ከፍለው መታከም ለማይችሉ የነጻ የሕክምና አገልግሎት ይሰጣሉ። የሕክምና አገልግሎት መስጠት የሚችል በርካታ ባለሙያዎችን አሰልጥነው አብቅተዋል።

ዶክተር አይነር ኤሪክሰን በኢትዮጵያ ቆይታቸው በርካታ ኢትዮጵያዊያንንም የሙያው ባለቤት አድርገዋል። አብረዋቸው የሚሰሩ ባልደረቦቻቸው ስለ እሳቸው ለመግለጽ ቃላት እያጠራቸው ርህራሄ፣ አጋዥነት እና ተባባሪነት መለያቸው ነው ይሏቸዋል።

ሙያቸውን ለሌሎች እንዳካፈሉ የሚናገሩት ዶክተር አይነር ኤሪክሰን ስራ በጀመሩበት በመጀመሪያዎቹ አምስት ዓመታት ብቁ የቃጠሎ አደጋ ሕክምና የሚሰጡ ባለሙያዎችን እንዳበቁ ይናገራሉ። በዚህም በአሁኑ ወቅት ከ50 እስከ 55 የሚደርሱ የቃጠሎ ሕክምና መስጠት የሚችሉ ባለሙያዎች አሉን፤ ከዚህ በላይ ለእኔ ደስታ የለም ሲሉም ይገልጻሉ።