በኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ በዝንጀሮ ፈንጣጣ የተያዘ ሰው የለም- ጤና ሚኒስቴር

ነሀሴ 8/2016 (አዲስ ዋልታ) በኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ በዝንጀሮ ፈንጣጣ (MPox) የተያዘ ሰው አለመኖሩን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የአፍሪካ ሲዲሲ ባወጣው መግለጫ፣ በ13 የአፍሪካ ሀገራት፣ 2 ሺህ 863 ሰዎች በዝንጀሮ ፈንጣጣ መያዛቸው እና፤ 517 ሰዎች ደግሞ በበሽታው መሞታቸው መረጋገጡን ጠቅሶ በሽታው የህብረተሰብ ጤና አህጉራዊ ደህንነት ስጋት መሆኑን ገልጿል።

የበሽታውን ስርጭት ለመከላከል የሁሉም የአፍሪካ ሃገራት የጋራ እርምጃን የሚጠይቅ መሆኑም አሳስቧል።

በአገራችን ኢትዮጵያ በቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ እና ሞያሌን ጨምሮ ሌሎች የመግቢያ ቦታ ላይ የቁጥጥርና ማጣራት ስራ እየተሰራ ሲሆን ጉዳዩን ጤና ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከሚመለከታቸዉ አካላት ጋር በመሆን በቅርበት እየተከታተሉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዝንጀሮ ፈንጣጣ የተያዙ ህሙማን የሚያሳዩዋቸው ዋና ዋና ምልክቶች እንደ ትኩሳት፣ ራስ ምታት፣ የዕጢ እብጠት፣ የጡንቻ እና የጀርባ ህመም፣ ሽፍታ፣ የቆዳ ቁስለት እንዲሁም የአቅም ማጣት ናቸዉ።

እነዚህ ምልክቶች መከሰታቸው የተረጋገጠ እና በቅርቡ በሽታው ወደ ተከሰተባቸው ሀገሮች የጉዞ ታሪክ ያለዉ ማንኛውም ሰው በአቅራቢያው ወደሚገኝ የጤና ተቋም በመሄድ አስፈላጊዉን ምርመራና እንክብካቤ ማግኘት እንዳለበትም ሚኒስቴሩ አሳስቧል።

በሽታው በቀጥታ ከሰው ወደ ሰው በንክኪ የሚተላለፍ እንደመሆኑ መጠን በመግቢያና መውጫ ኬላዎች አካባቢ ሕብረተሰቡን ያሳተፈ የተጠናከረ የቁጥጥርና መከላከል ስራዎች ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል፡፡