ቢሾፍቱ

ቢሾፍቱ

የኢትዮ-ጅቡቲን የባቡር መስመር ዝርጋታ ተከትሎ በ1917 ዓ.ም እንደተቆረቆረች የሚነገርላት ቢሾፍቱ በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን የምትገኝ ከተማ ስትሆን ከአዲስ አበባ በ47 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ትገኛለች።

ከባህር ጠለል በላይ 1 ሺሕ 920 ሜትር አማካኝ ከፍታ እና ወይናደጋ የአየር ፀባይ ያላት ቢሾፍቱ ስያሜዋን ያገኘችው “ቢሻን ኦፍቱ” ከሚለው የኦሮምኛ ቃል ሲሆን ትርጉሙም “ውሃ የሞላባት” ማለት ነው።

የረር፣ ባቦጋያ፣ ሀደው እና ኤባዩ በሚባሉ ተራሮች የተከበበችው ቢሾፍቱ ወደ ሰባት የሚደርሱ ሀይቆችን በውስጧ የያዘች ሲሆን ቢሾፍቱ፣ ባቦጋያ፣ ሆራ አርሰዴ፣ ኪሎሊ፣ ጨለለቃ፣ ኩሪፍቱ እና በልበላ ደግሞ ስያሜያቸው ነው።

ቢሾፍቱ በዘጠኝ የከተማ እና በአምስት የገጠር ቀበሌዎች የተዋቀረች ከተማ ስትሆን ታዋቂ ከሆኑ የሰፈር ስያሜዎቿ መካከል ሰርክል፣ 60 ማዞርያ፣ እጥቤ፣ ዝቋላ፣ ለምለም፣ ጌትሸት እና ሰንሻይን ይገኙበታል።

የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና ቢሮ የሚገኝባት ቢሾፍቱ በርካታ የሥልጠናና የምርምር ማዕከላት ያሏት ሲሆን የአየር ኃይል አካዳሚን ጨምሮ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የእንስሳት ሕክምና ፋኩልቲ፣ ብሔራዊ የእንስሳት ሕክምና ኢንስቲትዩት እና ቢሾፍቱ የግብርና ምርምር ማዕከል በከተማዋ ይገኛሉ።

በሆቴል እና ቱሪዝም የምትታወቀው ቢሾፍቱ በከተማዋ የሻምበል ለማ ጉያ አርት ጋለሪን ጨምሮ የተለያዩ ሆቴል እና ሎጆች የሚገኙ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ ፒራሚድ፣ ባቦጋያ፣ አይ ቪ ዩ፣ ጎልድ ማርክ ኢንተርናሽናል፣ አሻም አፍሪካ፣ ኩሪፍቶ ሪዞርት እና ወተር ፓርክ ተጠቃሽ ናቸው።

በከተማዋ ቢሾፍቱ አውቶሞቲቭን ጨምሮ ኢስት አፍሪካ ላዮን ማኑፋክቸሪንግ፣ ሳዋያ ፉድ ማኑፋክቸሪንግ፣ ሊዮስ ዘይት እና የሶያ ፋብሪካ፣ ኪያ የታሸገ ውሃ ማምረቻ፣ ሼባ ስቲል እና ሌሎች የተለያዩ ኢንዱስትሪዎች ይገኛሉ።

ቢሾፍቱ በየዓመቱ መስከረም ወር ላይ የሚከበረው እና በዩኔስኮ የማይዳሰሱ ቅርሶች የተመዘገበው የኢሬቻ በዓል በድምቀት የሚከበርባት ከተማ ስትሆን ይህም ሆራ አርሰዴ ላይ በመሰባሰብ የሚደረግ የምስጋና ስርዓት ነው።

ከተማዋ ጥቂት የማይባሉ የሀገር ባለውለታዎችን ያፈራች ሲሆን ከእነርሱም ውስጥ የትምህርት ሚኒስትር ብርሀኑ ነጋን (ፕ/ር) ጨምሮ አርቲስት ሻምበል ለማ ጉያ፣ አትሌት ዳዊት ወልዴ፣ አርቲስት አማኑኤል ሀብታሙ፣ የቀድሞ የብሔራዊ ቡድን ተጫዋች የነበረው አዲስ ህንፃ እና ሌሎችም ተጠቃሽ ናቸው::

በዚህች ውብ ከተማ ተወልዳችሁ ያደጋችሁም ሆነ በተለያየ አጋጣሚ አይታችኋት ልዩ ትዝታን ያተረፋችሁ ትውስታችሁን አጋሩን።
መልካም ሳምንት!

በአዲስዓለም ግደይ
#ከተሞቻችን