የከፍተኛ ትምህርትን ውጤታማነት የሚያሻሽል የዘርፍ ፖሊሲና ስትራተጂ ተዘጋጅቷል ተባለ

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተማረ ሰውን ከማፍራት ባለፈ ይበልጥ ውጤታማ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል የዘርፍ ፖሊሲና ስትራተጂ መዘጋጀቱን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቁ።

ነባሩ የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ ያለበትን ክፍተት ለመፍታትም በረቂቅ ደረጃ የኢትዮጵያ የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቶ የፖሊሲ ማሻሻያ የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ እንደሚገኝም ተመላክቷል።

በአዳማ ከተማ እየተካሔደ ባለው የዩኒቨርሲቲዎች ስትራቴጂክ እቅድ የግምገማ መድረክ ላይ ሚኒስትር ዴኤታው ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ በተለይም ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የአገርን የብልጽግና ጉዞ ለማሳካት እንዲችሉ የሚመሩበት የዘርፍ ፖሊሲና ስትራተጂ ተዘጋጅቷል።

ተቋማቱ የተማረ የሰው ኃይል ከማፍራትም ባለፈ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ውጤቶችን መርጦ በማምጣት፣ በማፍራትና በማላመድ ህብረተሰቡን ለማገልገል የሚያስችል ስራ እንዲያከናውኑ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም አስረድተዋል።

እያጋጠሙ ያሉ ክፍተቶችን ከመሙላት አኳያም ቀደም ሲል 70/30 የነበረው የከፍተኛ ትምህርት የተፈጥሮ ሳይንስና ማህበራዊ ሳይንስ የቅበላ መርሃ-ግብር እንዲቀር በማድረግ 55/45 እንዲሆን መደረጉም ተጠቁሟል።