የደቡብ ዕዝ በተለያዩ ዘመቻዎች ድጋፍ ላደረጉ አካላት እውቅና ሰጠ

ጥር 24/2014 (ዋልታ) የደቡብ ዕዝ በህግ ማስከበር፣ በኅልውና እና በኅብረ ብሔራዊ ለአንድነት ዘመቻዎች ድጋፍ ላደረጉ ተቋማትና የኅብረተሰብ ክፍሎች የእውቅናና የምስጋና የምስክር ወረቀት ሰጠ።

ዕዙ ባዘጋጀው የሽልማት ሥነ-ስርዓት እውቅና የተሰጣቸው የአፋር ክልል፣ የሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት፣ የእስልምና ጉዳዮች፣ የሰሜን ወሎ ዞን ወልዲያ፣ ራያ ቆቦ፣ ሀብሩ ወረዳ እና ሌሎች መስተዳድሮችም የተዘጋጀላቸውን የምስክር ወረቀት እና የዋንጫ ሽልማት ከሌተናል ጀነራል ሰለሞን ኢተፋ እጅ ተቀብለዋል።

ጄኔራል መኮንኑ ‘‘አሸባሪውን ኃይል ለመደምሰስ በተደረገው ትግል ለሠራዊታችን ያደረጋችሁት መስዋዕትነት እስከ መክፈል የደረሰ ጀግንነት ምስጋና ይገባችኋል’’ ብለዋል።

የሰሜን ወሎ ዞን መስተዳድር በበኩሉ ዕዙ ባካሄደው የጀግና ሜዳይ አሰጣጥ ሥርዓት ላይ ለተገኙ የክብር እንግዶች ለጄኔራልና ለሌሎች ከፍተኛ መኮንኖች የራያ የባህል ልብስ ስጦታ አበርክቷል።

ሽልማቱ ከተበረከተላቸው መካከል በቆቦ ወረዳ የጉራ ወርቄ ቀበሌ ሕዝባዊ ሚሊሻዎች ከአሸባሪው ሕወሓት ጋር ባደረጉት ውጊያ አካባቢያቸውን ያላስደፈሩ ጀግኖች መሆናቸው ተገልጿል።

የወርቄ ቀበሌ አባ-ሀጋ በካሪስ ጎቤ የተሰጠን እውቅና በቀጣይም ከሰራዊታችን ጎን ተሰልፈን አሸባሪውን ለመደምሰስ የሞራል ድጋፍ ይሆነናል ማለታቸውን ከመከላከያ ሰራዊት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።