ጤና ደጉ – የደንጊ በሽታ ምልክቶችን መከላከያ መንገዶች

የደንጊ በሽታ በቫይረስ አማካኝነት ከወባ ትንኝ ወደ ሰው የሚተላለፍ በሽታ ነው። በሽታው ሞቃታማና ከፊል ሞቃታማ በሆኑ የዓለም ክፍሎች የሚከሰት ሲሆን በተለይ በከተሞችና ከተማ ቀመስ አካባቢዎች በብዛት ይገኛል።
ግማሹ የዓለማችን ክፍል በበሽታው ስጋት ውስጥ የሚገኝ ሲሆን በዓመት ከ100 እስከ 400 ሚሊዮን ህዝብ በቫይረሱ ይለከፋል።
በሽታው በአፍሪካ ዋና የህብረተሰብ የጤና ችግር አለፍ ሲልም የኢኮኖሚ ችግር ስለመሆኑ የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።
የደንጊ እና በምልክቶቹ እሱኑ የሚመስለው የችኩንጉንያ በሽታ በአገራችን ስለመኖራቸው የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ይጠቁማል።
የበሽታው ምልክት፡-
በቫይረሱ ከተለከፍን ከ4 እስከ 10 ባሉት ቀናት ውስጥ ምልክቶች የሚታዩ ሲሆን ከ2 እስከ 7 ቀናት ያክል ሊቆይና ከ20 ሰዎች በአንዱ ላይ በሽታው ሊጠናበት እንደሚችል ብሎም እስከ ሞት ሊያደርሰው ይችላል።
ለመጀመሪያ ጊዜ በበሽታው የተያዘ ሰው ከሚያሳያቸው ምልክቶች ውስጥ፡-
• የጡንቻና መገጣጠሚያ ህመም
• ከፍተኛ ትኩሳት
• ሽፍታ
• የድካም ስሜት
• ከዓይናችን ጀርባ ህምም መሰማት
• ራስ ምታት
• ማቅለሽለሽና ማስታወክ
• የዕጢዎች ማበጥ
በበሽታው ለሁለተኛ ጊዜ የተለከፈ ሰው ህመሙ ሊጠናበት ይችላል ይላል የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ። ይህን ተከትሎም ከፍ ያለ የወገብ ህመም፣ የማያቋርጥ ማስመለስ፣ ቶሎ ቶሎ መተንፈስ፣ የአፍንጫና ድድ መድማት፣ ድካም፣ ደም የተቀላቀለበት ማስታወክና ማስቀመት፣ ውሃ ጥም፣ መገርጣትና የድካም ስሜት ሊሰማን ይችላል።
ህክምናው፡-
በሽታውን ራሱኑ አክሞ ማዳን ባይቻልም ምልክቶቹን ግን ማከምና እንዲቀንሱ ማድረግ ይቻላል። ከዚህ በተጨማሪ በቂ ረፍት ማድረግ፣ በቂ ፈሳሽ መጠጣት እና ማስታገሻ (አስፕሪን አይመከርም) መድኃኒት መውሰድ ይመከራል።
መከላከያ መንገዶች፡-
በሽታውን ለመከላከል ሊወሰዱ ከሚችሉ እርምጃዎች ውስጥ የወባ ትንኝ ለመራባት የሚያመቹ ቦታዎችንና ሁኔታዎችን ማጥፋት አንዱ ነው። ለረጅም ጊዜ የተከማቸ ውሃን ማስወገድ፣ የውሃ ማጠራቀሚያዎችን መክደን፣ እንደ ጎማ እና ጎድጓዳ እቃዎችን በአግባቡ መጠቀም፣ እጅና እግርን የሚሸፍኑ ልብሶችን መልበስ፣ ስንተኛ በጸረ-ትንኝ ኬሚካል የተረጨ የአልጋ አጎበር መጠቀም ይገባል። ከላይ የተጠቀሱ ምልክቶችን ሲያዩ ባፋጣኝ ወደ ጤና ተቋም መሄድ ይመከራል።
ምንጭ -WHO, CCD MoH, BMC Infectious Disease
በቴዎድሮስ ሳህለ