የፓሪስ ኦሊምፒክ አስደናቂና አነጋጋሪ ክስተቶች


በ33ኛው የፓሪስ ኦሊምፒክ በ19 ቀናት ቆይታው በርካታ አዳዲስ እና እንግዳ ሁነቶችን አስተናግዶ ዛሬ ይጠናቀቃል።

በውድድሩ በርካታ አስደናቂ፣ አስደንጋጭ እና ተንኳሽ ድርጊቶች የተስተናገዱበት እንደነበር ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ዘግበውት አልፏል።

የፓሪስ ኦሊምፒክ እንደ ቤጂንግ ወይንም እንደ ለንደን ኦሊምፒክ ብዙም ካለመድመቁ ባሻገር ብዙ ሰዎችን ያስቆጡ ድርጊቶች እና የዝግጅት ጉድለቶች የተስተናገዱበት ነበር። የተመረጡ የውድድሩ ክስተቶችን ከዚህ በታች ለመዳሰስ እንሞክራልን።

    የፈረንሳይ ባቡር መጓጓዣ መስመር ጥቃት

ፈረንሳይ ዓለም በጉጉት የምትጠብቀውን ትልቁን ድግስ በድምቀትና በሰላም ለማከናወን ሽር ጉድ ስትል ነበር የሰነበተችው። በቅድመ ውድድር ከፍተኛ ትኩረት ከተሰጣቸው ጉዳዮች አንዱ ጸጥታና ደህንነት ሲሆን ከ46 ሺህ በላይ ፖሊሶችን እና ልዩ ልዩ የጸጥታ ተቋማትን አሰማርታ ነበር።

የድሮን መጥለፊያ ሳይቀር የረቀቁ የስለላና ክትትል ቴክኖሎጂዎችን ጥቅም ላይ ብታውልም በመክፈቻው ዕለት በባቡር መስመሮቿ ላይ የተቃጣውንና ከ800 ሺህ በላይ የሚሆኑ ተጓዦችን ጉዞ ያስተጓጎለ ጥቃት ማስቆም አልቻለችም።

ድርጊቱ ከፍተኛ ድንጋጤ ከመፍጠሩም በላይ መስመሩን ወደ አገልግሎት ለመመለስና በአስተማማኝ መልኩ ጥቃቱን ለመመከት በርካታ ቀናት ወስዶባታል። ኃላፊነት የወሰደውን አካልም ማንነት በወጉ ለመለዬት አለመቻሉ ፈረንሳይን ትዝብት ላይ የጣለና ድግሷን ከጅምሩ ያበላሸ ድርጊት ሆኖ አልፏል።

   በመክፈቸው ላይ የቀረበው ኃይማኖትን የሚተነኩስ ድርጊት

በከፍተኛ የጸጥታ ስጋት ውስጥ ሆኖ የተካሄደው የመክፈቻ ስነስርዓት ሌላ ውዝግብ ይዞ ብቅ አለ። ድርጊቱ በክርስትና ኃይማኖት ተከታዮች ዘንድ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠውን “የመጨረሻው ራት” የተባለውን ሁነት በሚተነኩስ መልኩ የመድረክ ሁነት ቀርቦ በርካታ የዓለም አብያተ ክርስቲያንን አስቆጣ፤ ድርጊቱን ኮንነው መግለጫም አወጡ።

ከክርስቲያን ዕምነት አለፍ ሲልም የእስልምና እምነት ተቋማት ጭምር ድርጊቱን ኮንነው መግለጫ እስከማውጣት የደረሱበት ነበር፡፡ ታዋቂ ግለሰቦችና መሪዎች ጭምር ድርጊቱን ፈር የለቀቀና ተንኳሽ ሲሉ ቁጣቸውን አሰሙ።

    የዋና መወዳደሪያው የሴኔ ወንዝ መቆሸሽ

ከቤት ውጭ ለሚካሄድ የዋና ውድድር የተመረጠውና ፓሪስ መሃል ለመሃል ሰንጥቆ የሚያልፈው የሴኔ ወንዝ ንፅህና ጉዳይ አንዱ ነበር። ውሃው ከመቆሸሹ የተነሳ ለማየት እንኳን ደስ የማይል በመሆኑ በዓለም ስፖርት ቤተሰብ ዘንድ አነጋጋሪ ሆኖ ነበር።

ፓሪስ የወንዙን ንፅህና ለማረጋገጥ በቢሊዮን የሚቆጠር ዩሮ መድባ ብትሰራም ስፖርተኞችን ጥያቄ በአሳማኝ ሁኔታ መመለስ አልቻለችም። የከተማዋ ከንቲባና ባለስላጣኖች ጭምር ወንዙ ውስጥ ገብተው በመዋኘት የማሳመንና የማግባባት ስራ እስከመስራት ደርሰዋል።

በኋላም በውድድሩ ወቅት እንደታየው እስከዛሬ ከተካሄዱ የቤት ውጭ የውሃ ዋና ውድድር ቦታዎች ድፍርስና ለመዋኘት ቀርቶ ለማየት ደስ የማይል እንደነበር ዓለም ታዝቧል።

   በአምስት ተከታታይ የኦሊምፒክ ውድድሮች 5 ወርቆችን ያሸነፈው ኩባዊ

በፓሪስ ኦሊምፒክ በልዩ ልዩ ውድድሮች በርካታ አስገራሚና አስደናቂ ብቃት ያላቸው አትሌቶችን ለማየት አስችሎናል። በእድሜ ወጣትና አንጋፋ፣ በብዙ ዘርፍ የተወዳደሩ ወዘተ አትሌቶች ያዬንበት ነበር የፓሪስ ኦሊምፒክ።

ከነዚህ ውስጥ ግን የ41 ዓመቱ ሚሄይን ሎፔዝ አንዱ ነው። ይህ ኩባዊ አትሌት በግሪኮ-ሮማ የትግል ዘርፍ ተወዳድሮ ለአገሩ ወርቅ አስገኝቷል። አትሌቱን የተለዬ ያደረገው ነገር ቢኖር እስከዛሬ በተሳተፈባቸው ተከታታይ አምስት ኦሊምፒኮች አምስት ወርቅ ማሸነፉ ነው።

አትሌቱ በቤጂንግ፣ በለንደን፣ በሪዮ፣ በቶኪዮና አሁን ደግሞ በፓሪስ ኦሊምፒክ በተከታታይ ተወዳድሮ ያገሩን ባንዲራ በዓለም አደባባይ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ አድርጓል።

   የልጀሪያዋ ቡጢ ተወዳዳሪ ጾታ ጉዳይ

በፓሪስ ኦሊምፒክ ከተስተናገዱ አጨቃጫቂና አከራካሪ ጉዳዮች አንዱ የአልጀሪያዊ ቡጢ ተወዳዳሪ ጾታ ጉዳይ ነበር። በውድድሩ የወርቅ ሜዳልያ ያሸነፈችው ኢማን ከሊፍ በመጀመሪያ ግጥሚያዋ የጣሊያናዊት ተጋጣሚዋን በ46 ሰከንዶች አቋርጣ እንድትወጣ አድርጋታለች። ጣሊያናዊቷ ተጋጣሚ “የሴት ቡጢ አይደለም የተመታሁበት፤ አልቻልኩም ” የሚል መልዕክት ማስተላለፏን ተከትሎ  የአትሌቷ ተክለ ሰውነትና ጾታ ዓለምን ለሁለት ከፍሎ አከራክሮ አልፏል። ኢማንም ሴት ተጋጣሚዎቿን አንድ በአንድ እየዘረረች የወርቅ ባለቤት ሆናለች።

    አነጋጋሪው የቱርክ የተኩስ ተወዳዳሪ አዛውንት

የ58 ዓመቱ የቱርክ የተኩስ ተወዳዳሪ ዩሱፍ ዲኬክ የፓሪስ ኦሊምፒክ ክስተት በመሆን ማህበራዊ ሚዲያ ከተቆጣጠሩት አትሌቶች ቀዳሚው ነበር፡፡

ሰውዬው በዕድሜው አንጋፋነት ብቻም ሳይሆን በውድድሩ ላይ የተኩስ ተወዳዳሪ አትሌቶች የሚጠቀሙባቸውን የኢላማ ማጥሪያ መነፅር፣ የአይን መሸፈኛም ሆነ የተለዬ ቁሳቁስ ሳይጠቀም ዘና ብሎ በመተኮስ የተፈለገውን ኢላማ በመምታት አጃኢብ አስብሏል። በውድድሩም ለአገሩ የብር ሜዳልያ አስገኝቶላታል።

በተኩስ ላይ እያለ የተለቀቀው ፎቶው በማህበራዊ ሚዲያ ተሰራጭቶ ፖስተሮች፣ የቪዲዮ ጌሞች የስዕል ንድፎችና ለንቅሳት መስሪያ ጥቅም በመዋል የብዙዎችን ቀልብ ስቧል። በሙያው መካኒክ መሆኑ የተገለጸው ቱርካዊው አትሌት በውድድሩ ወቅት ዘና ብሎ በመቅረቡ ጭምር ታዳሚን አስደምሟል።

    አራት አዳዲስ ውድደሮች መጨመር

በፓሪስ ኦሊምፒክ አራት አዳዲስ ውድድሮች የተካተቱበት መድረክ ነበር። ስኬትቦርድ፣ ሰርፊንግ፣ የብሬክ ዳንስና ፈጣን የግድግዳ መውጣት ውድድሮች ናቸው በ2024 የፓሪስ ኦሊምፒክ የተካተቱት።

በውድድር መድረኩ የዓለም ስፖርት ታዳሚያንን ቀልብ የሳቡ በርካታ ጉዳዮች ተስተናግደውበት ዛሬ ምሽት ፍጻሜውን ያገኛል።

በቴዎድሮስ ሳህለ