ገለልተኝነት የራቀው ‹ገለልተኛው ተቋም

በነስረዲን ኑሩ
ታኅሣሥ 8/2014 (2014) ዛሬ የተባበሩት መንግሥታት የሰብኣዊ መብቶች ምክር ቤት ከተቋቋመለት ዓላማ ውጪ በሆነና በማይመለከተው ጉዳይ ገብቶ የፖለቲካ አጀንዳን ለማስፈፀም ቀጠሮ ይዟል፡፡
ምክር ቤቱ የስብሰባውን መጠራት ያልፈቀደችውን አፍሪካ ዘንግቶ፤ በአንዲት አፍሪካዊት የነፃነት ምልክት በሆነች አገር የውስጥ ጉዳይ ገብቶ ሊያቦካ ተሰናድቷል፡፡
ለዚህ መንደርደሪያ ደግሞ እነአምነስቲ ኢንተርናሽናል አህያውን ፈርቶ ዳውላውን እንዲሉ በገባባቸው ቦታዎች ሁሉ የዘር ጭፍጨፋን እየፈፀመ ያለውን የአሸባሪው ሕወሓት ወንጀል ችላ ብለው ‹በምዕራብ ትግራይ የጦር ወንጀል እየተፈፀመ ነው› የሚል ድምዳሜን ጥቂት ሰዎችን በስልክ አናግሮ ያጠናቀረውን የፈጠራ ሪፖርት አውጥቷል፡፡ ይህ ደግሞ ለሽብርተኛው አፎች ሰርግና ምላሽ ሆኗል፡፡
ምዕራባዊያኑ አፍሪካን በቅኝ ግዛት ለመቀራመት በርሊን ላይ ሲመክሩና የበርሊኑን ስምምነት ሲያጸድቁ የመምከሪያ አዳራሹ በር ለአፍሪካ እና አፍሪካዊያን ዝግ ነበር፡፡
በርሊን ላይ በተደረሰው የቅርጫ ስምምነት መሰረት ኢትዮጵያ ለጣሊያን ታጭታ ነበር፡፡
ቅኝ ገዢዎቹ በዚያ አዳራሽ ውስጥ ባስቀመጡት ቀመር መሰረት አብዛኛዎቹን የአፍሪካ አገራት በቅኝ ገዢነት ተቀራምተው ሃብታቸውን መዝረፍና ሕዝባቸውን መበዝበዝ የቻሉ ቢሆንም በኢትዮጵያ በኩል የመጣው ወራሪ ግን ሊሳካለት አልቻለም፡፡
የኢትዮጵያን በተፈጥሮ ሃብቶች የበለጸገ ምድር ለመበዝበዝ ቋምጦ የመጣው የፋሺስት ጣሊያን ጦር በጀግኖቹ እና ልባሞቹ የኢትዮጵያ ልጆች አይሆኑ ሆኖ ሲመለስ እግረመንገዱን ለምዕራባዊያን እና ለመላው ዓለም አንድ መልዕክት ይዞ ነበር የተመለሰው፡፡
ይኸውም ኢትዮጵያ ምንም ደሃ እና የጥቁር ሕዝብ አገር ብትሆንም ለቅኝ ግዛት ግን የማትንበረከክ መሆኗን የሚገልጽ ነው፡፡
ታሪክ ራሱን ደገመ እንዲሉ ፅንፈኛ የሆኑት አንዳንድ ምዕራባዊያን እና መሪያቸው አሜሪካ ዛሬም ከብዙ ዓመታት በኋላ የአፍሪካዊት አገርን ጉዳይ ያለአፍሪካዊያን ፍላጎት በመምከር ያንን ያረጀ እና ያፈጀ አካሄዳቸውን ለመድገም እየተጋጋጡ ይገኛሉ፡፡
እነ አሜሪካ እና በእሷ የሚዘወሩ ምዕራባዊያን አገራት እንደፈለጋቸው የሚጠመዝዙት የተባበሩት መንግሥታት በስሁት ውሳኔዎቹ የበርካታ ሉኣላዊ አገራትን ኅልውና ተዳፍሯል፡፡
ይህን የተረዱ የአፍሪካ አገራት የሁሉም የሆነው የተባበሩት መንግሥታት በተለይም የፀጥታው ምክር ቤት የአፍሪካዊያን ቋሚ መቀመጫ ሊኖረው ይገባል የሚለውን ጥያቄ ማቅረብ ጀምረው፤ ጉዳዩ ወደ ንቅናቄነት ከፍ እያለ ነው፡፡
ፍጹም ባለተረጋገጠ እና በበሬ ወለደ ትርክት ኢራቅ እና ሊቢያ የዘመተው አሜሪካ መራሹ የኔቶ ጦር ንጹሃን ዜጎችን ለሞት፣ ስደትና እንግልት ሲዳርግ አገራቱን ሙሉ በሙሉ በማወደም አይ ኤስ አይ ኤስን የመሳሰሉ የሽብር ቡድኖች መፈንጫ አርጓቸዋል፡፡
ሊበሏት ያሰቧትን አሞራ እንዲሉ እጇን ለማስጠምዘዝ ያለፈቀደችውን ኢትዮጵያ ባለዋለችበት እየከሰሷት እና የማዕቀብ ናዳ እያወረዱ ሊያፍረከርኳት ያልተቆጠበ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡
በተለይ አሸባሪው ሕወሓት ድል እያደረገ ሲመስላቸው በኢትዮጵያ እየሆነ ያለውን ለመስማት የዝሆን ጆሮ ስጠኝ የሚሉት እነዚሁ አገራትና ተቋማት መንግሥት ከመከላከል ወደ ፀረ ማጥቃት ገብቶ በቀናት ውስጥ አንጸባራቂ ድሎችን ሲቀዳጅ እና የሽብሩ ቡድኑ አፍንጫ እዚህ ሲመታ ከዚያ ማዶ የእነርሱ አይን ማልቀስ ይጀምራል፡፡
ይህ ሲሆን የሰብኣዊ መብት መጣስ የሚለው አጀንዳ ይራገባል፤ የዴሞክራሲ እጦት የመልካም አስተዳደር ችግር ያሳስባቸዋል፤ የመግለጫ እና ዕቀባ ጋጋታ ማስፈራሪያ ሆኖ ይዥጎደጎዳል፡፡
የዚሁ ዘመቻ አካል የሆነውና ዛሬ በጄኔቫ የሚካሄደው የተባበሩት መንግሥታት የሰብኣዊ መብቶች ምክር ቤት የጠራው ልዩ ስብሰባ አንድ ሦስተኛውን ቁጥር የሚይዙትን የድርጅቱ አባል የሆኑ የአፍሪካ አገራትን በማግለል በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ውሳኔ እንደሚያሳልፍ እየተጠበቀ ነው፡፡
ልዩ ስብሰባው እንዲጠራ ሲጎተጉት ሰንብቶ የተሳካላትን የአውሮፓ ኅብረት ጥያቄ በመቀበል ፊርማቸውን ካኖሩት መካከል አንድም አፍሪካዊ አገር አለመኖሩ ግን የሚያስተላልፈው መልዕክት ከፍ ያለ ነው፡፡
በዛሬው ልዩ ስብሰባም ድምፅ እንደሚሰጡ ከሚጠበቁት 47 አገራት ውስጥ የአፍሪካ አገራትና ሌሎች ለእውነት የቆሙ ኃይሎች ከኢትዮጵያ ጎን እንደሚቆሙ ይጠበቃል፡፡
የሆነው ሆኖ ኢትዮጵያ ግን በልዩ ስብሰባው የሚተላለፈውን ማንኛውንም ውሳኔ አልቀበልም ስትል ከወዲሁ ይፋ አድርጋዋለች፡፡
የኢትዮጵያ ሰብኣዊ መብቶች ኮሚሽንም ግልፅ ደብዳቤን ያወጣ ሲሆን የተባበሩት መንግሥታት የሰብኣዊ መብቶች ምክር ቤት አካሄድ ከዚህ ቀደም በኮሚሽኑና በመንግሥታቱ የሰብኣዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽነር የተደረገውን ጥምር ምርመራ እውቅና የሚነፍግ ነው ሲል ተቃውሟል፡፡
ምክር ቤቱ መስራት የነበረበት የጋራ ጥምር ሪፖርቱ ምክረሐሳቦች እንዲተገበሩ ድጋፍ ማድረግ እንጂ በራሱ ተቋምም ተሳትፎ ጭምር የተደረገን ሃቀኛ ምርመራ ትቶ ሌላ አጀንዳ ለመቅረፅ መሞከር እንዳልነበርም አሳውቋል፡፡
እዚህ ላይ ዋናው ቁምነገር የተባበሩት መንግሥታት ገለልተኛ ስለመሆኑ ጥያቄዎች እየተነሱበት ከመሆኑም ባሻገር በቀጣዮቹ ጊዜያት ተቀባይነቱ እና ተደማጭነቱ እንደሚያሽቆለቁል ጠቋሚ ነው፡፡
ስብስቡ የአውሮፓ ኅብረት እና የአሜሪካ ፍላጎቶችን እና የፖለቲካ አጀንዳዎች ማስፈጸሚያ ሆኖ እያገለገለ ነው በሚል እየተወቀሰም ይገኛል፡፡ በተግባርም እያደረገው ነው፡፡
ይህ የመንግሥታቱ አግላይ አካሄድ በፍጥነት እየበለጸጉ ያሉ እና የአንድ አካል ፈላጭ ቆራጭነት ዘመን አብቅቷል ብለው በሚያኑ ቻይና እና ሩሲያን በመሳሰሉ አገራት ዘንድም ተቀባይነትን እያጣ ነው፡፡
ይህ ደግሞ ሄዶ ሄዶ ምናልባትም ለድርጅቱ ኅልውና አደገኛ ሊሆን ይችላል እየተባለ ነው፡፡