ሀገሬ-የዘንገና ሀይቅ – ማራኪው የተፈጥሮ መስህብ

የዘንገና ሀይቅ


የዘንገና ሀይቅ በሚያስደንቅ ተፈጥሯዊ ገፅታው የጎብኚዎችን ቀልብ በመግዛት የሚታወቅ ነው። ሀይቁ በአማራ ክልል በአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን ይገኛል።

ይህ ውብና ማራኪው የተፈጥሮ መስህብ ከመዲናዋ አዲስ አበባ በ430 ኪሎ ሜትር እንዲሁም ከክልሉ ርዕሠ ከተማ ባህርዳር በ127 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል።

ከእንጅባራ ከተማ በስተደቡብ ምሥራቅ በ6 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ሲሆን ከፍታው ከባህር ጠለል በላይ 2ሺሕ 515 ሜትር ነው።

በጉድጓዳማ ቦታ የሚገኘው እና የክብ ቅርፅ የያዘው ይህ ሀይቅ ዜሮ ነጥብ 54 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ስፋት እንዳለውም ይጠቀሳል።

ከሰሜን ወደ ደቡብ 970 ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን ከምስራቅ ወደ ምዕራብ ደግሞ 930 ሜትር ይረዝማል።

የአገው ፈረሰኞች በዓል ገፅታ


ይህ ውብ የተፈጥሮ ሀይቅ በእሳተ ገሞራ እንደተፈጠረ የሚገለጽ ሲሆን በአማካይ ከ150 እስከ 169 ሜትር ጥልቀት እንዳለው መረጃዎች ያሳያሉ።

በባንጃ ወረዳ በከሳ ቸውሳ ቀበሌ በውብ መልክአ ምድር አቀማመጥ ታጅቦ የሚታየው ሀይቁ መንፈስን በሚያድስ ተፈጥሮም ታድሏል።

ሐይቁ ሁለት ዓይነት የዓሣ ዝሪያዎች መገኛም ነው። የተለያዩ አዕዋፍ ዝሪያዎችን መመልከትም የአከባቢውን የመስህብነት ፀጋን ያጎላዋል።

በሀይቁ ዙሪያ የተለያዩ የዱር እንሳስት የሚገኙ ሲሆን ጉሬዛ፣ ዓሣማ፣ ከርከሮ እና ዱክላ ይጠቀሳሉ።

በሀይቁ ዳርቻና በዙሪያው ከሚገኘ የተፈጥሮ ዕፅዋት ጋር ተዳምሮ የፀሀይ ብርሃን የሚፈጥረው ነፀብራቅ የሀይቁን መልክ ስለሚቀያይሩት ውስጥን የሚማርክ ዕይታን ያጎናፅፋል።

ከእንጅባራ ከተማ በእግርዎ አሊያም በመኪና የመንገዱን ግራና ቀኝ በከበቡ የተፈጥሮ እና ሰው ሠራሽ ዛፎች አየተደመሙ፣ በነፉሻማው አየር አእምሮዎን እያደሱ ወደ ውቡ ዘንገና ሀይቅ ይዘልቃሉ።

ሀይቁ የሚገኝበት ሥፍራ ከስፋልት መንገድ በቅርበት ላይ በመሆኑም የእግር ጉዞ ለሚያደርጉ ጎብኚዎች ምቹ ነው።

በዞኑ የተፈጥሮ እና ሰው ሠራሽ የመስህብ ሥፍራዎች የሚገኙ ሲሆን ቀልብን የሚማርኩ ፏፏቴዎች ዋሻዎች እና ሀይቆች ይገኛሉ።

ወደ አዊ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን ዘልቀው የዘንገናን ሀይቅ እና ሌሎች መስህቦችን ይጎብኙ አገርዎን ይወቁ!!

ቸር እንሰንብት!!

በሠራዊት ሸሎ