ሀገሬ-የጋምቤላ ብሔራዊ ፓርክ – ውብና የተፈጥሮ ጸጋ ባለቤት



የጋምቤላ ብሔራዊ ፓርክ በብዝሃ የተፈጥሮ ሀብቶች የታደለ ፓርክ ነው። በተፈጥሯዊ ውበቱ የሚያስደንቅ ዕይታን የተጎናፀፈው ብሔራዊ ፓርኩ 4 ሺሕ 575 ስኩዌር ኪ.ሎ ሜትር ይሸፍናል፡፡

ብሔራዊ ፓርኩ ከጎረቤት ሀገር ደቡብ ሱዳን ቡማ ብሔራዊ ፓርክ ጋር የሚዋሰን ሲሆን ከአዲስ አበባ 810 ኪ.ሎ ሜትር ተጉዘው ያገኙታል።

በለምለም ተፈጥሮ እና ከሰው ቁመት ይልቅ በሚረዝም ለምለም ሣር ውስጥ በሚርመሰመሱ የዱር እንስሳት እና አእዋፍት ክምችት የሚታወቀው ብሔራዊ ፓርኩ ከአጥቢ እንስሳት እስከ የአእዋፍ ዝሪያዎች በምድር የሚሳቡትን ጨምሮ በውሃ አካላት መኖሪያ ያደረጉ ግዙፍ የዓሣ ዝሪያዎች የሚገኙበት እና የተትረፈረፈ የተፈጥሮ ሀብት ክምችት ያለበት ነው።

በመሆኑም በየብስና በውሃ አካላት ተፈጥሮ የቸረችው እምቅ ፀጋው ለተለያዩ እንስሳት ምቹ መኖሪያ እንዲሆን አስችሎታል። ከእነዚህ የዱር እንስሳት መካከል የጋምቤላ ብሔራዊ ፓርክ መገለጫ የሆነው ነጭ ጆሮ ቆርኪን ጨምሮ አንበሳ፣ ዝሆን፣ ቀጭኔ፣ ጉማሬ፣ ጎሽ እና አጋዘን የሚጠቀሱ ናቸው። በዚህም ፓርኩ በውብ የመስህብ ስፍራዎች የታደለና ድንቅ የቱሪዝም መዳረሻ ነው፡፡

ፓርኩ 69 አጥቢ እንስሳት፣ 7 የተሳቢ እንስሳት ዝርያዎች፣ ከ97 በላይ የዓሳ ዝርያዎች እንዲሁም 327 የአእዋፍ ዝሪያዎች እና ከ420 የሚልቁ የዕጽዋት ዓይነቶች የሚገኙበት እና በተፈጥሮ ሀብቶች የተሞላ መሆኑን የተለያዩ መረጃዎች ያስረዳሉ።

ጥብቅ የተፈጥሮ ደን፣ በውስጡ አቋርጠው ክረምት ከበጋ የሚፈሱ ትላልቅ ወንዞች እና ዕይታን የሚማርኩ ሀይቆች የጋምቤላ ብሔራዊ ፓርክ መገለጫዎችም ናቸው።

የባሮ፣ የአኮቦ እና ጊሎ ወንዞች ፓርኩን አቋርጠው ከሚፈሱ ወንዞች ሲሆኑ እነዚህ ወንዞች የውሃ ቱሪዝምን ምርጫቸው ላደረጉ ጎብኚዎች ምቹ መዝናኛ ናቸው።

የፓርኩ ውበት ከሆኑት ወንዞች አንዱ የባሮ ወንዝ ሲሆን ፓርኩን ከደቡብ ሱዳን ጋር ያገናኛል። ወንዙ የመጓጓዣ አግልግሎት የሚሰጥ በመሆኑም ለጎብኚዎች አንዱ የቱሪዝም መዳረሻ ነው።

ዓመቱን በሙሉ ልምላሜ በማይለየው ተፈጥሮ የታደለው ውብ ምድር በአየርም ሆነ በምድር ፓርኩን ለሚጎበኙ ጎብኚዎች የህልና እርካታን የሚሰጥ የመስህብ ሥፍራ ነው።

የጋምቤላ ክልል እርጥበታማ በሆነው ሞቃት የአየር ንብረት የሚታወቅ ሲሆን የጋምቤላ ብሔራዊ ፓርክን ጨምሮ የተፈጥሮ፣ የሰው ሠራሽ እና ባህላዊ መስህቦች እንዲሁም ብዝሃ የተፈጥሮ ሀብት ክምችት ያለበት እና ድንቅ የቱሪዝም መዳረሻዎች የሚገኝበት ክልል ነው።

በጋምቤላ ክልል የሚገኙትን ውብ የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ የመስህብ ሥፍራዎችን ይጎብኙ ሀገርዎን ይወቁ።

ቸር እንሰንብት!!

በሠራዊት ሸሎ