መጋቢት 16/2013 (ዋልታ) – ለኢትዮጵያና ለአፍሪካ በኦሎምፒክ መድረክ በ10 ሺህ ሜትር የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ ላስገኘችው ኮማንደር አትሌት ደራርቱ ቱሉ መጋቢት 19 ቀን 2013 የእውቅና እና የምስጋና መርሐ ግብር በአዲስ አበባ እንደሚከናወን ተገለጸ።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ቢልልኝ መቆያ እንደገለፁት፣ መርሐ ግበሩን ማዘጋጀት ያስፈለገው ለአገር ውለታ የሰሩ ጀግኖችን በሕይወት እያሉ ለመዘከር ታስቦ ነው።
ደራርቱ በ10 ሺህ ሜትር ውድድር ለአፍሪካ የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ ያመጣች አትሌት በመሆኗ ለዚህ ፈር ቀዳጅ ድል ዕውቅና ለመስጠት መሆኑንም ገልፀዋል።
“ለአገራቸው ጉልበታቸውንና ዕውቀታቸውን የሚሰጡ ዕውቅና ሊሰጣቸው ይገባል” ያሉት አቶ ቢልልኝ፤ ደራርቱ በአትሌቲክሱ ብቻ ሳይሆን በበጎ አድራጎት ተግባርም ትልቅ ቦታ እንዳላት ጠቅሰዋል።
“አህጉራዊ ጀግና በመሆኗም ሌሎች የእሷን ዓርአያ እንዲከተሉ ለማነሳሳት የዕውቅና መርሐ ግብሩ በር ይከፍታል” ብለዋል።
በዕውቅና መርሐ ግብሩ የክልሎች ኃላፊዎች፣ የፌዴሬሽኑ አመራሮች፣ ሚኒስትሮች፣ ታዋቂ አትሌቶችና አርቲስቶች የተካተቱበት ከ600 በላይ ታዳሚዎች እንደሚገኙ ገልፀዋል።
አትሌት ደራርቱ ቱሉ እ.አ.አ 1992 የባርሴሎና ኦሊምፒክ ኢትዮጵያን በ10 ሺህ ሜትር ውድድር በመወከል በሴቶች ለኢትዮጵያና ለአፍሪካ የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳልያ አስመዝግባለች።
በተጨማሪም ለኢትዮጵያ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና፣ በዓለም አገር አቋራጭ ውድድሮችና ሻምፒዮናዎች ወርቅ፣ ብር፣ ነሐስና ዲፕሎማ ማስገኘቷን ኢዜአ ዘግቧል።