ሕግ ይዳኘኝ – ትዳሯን የፈታች ሴት ሌላ ጋብቻ ለመፈጸም የሚጣልባት ቀነ ገደብ

በኢፌዲሪ የፍትሐ ብሔር ሕግ መሰረት ጋብቻ አስራ ስምንት ዓመት የሞላቸው አንድ ወንድ እና አንዲት ሴት ተስማምተው በክብር መዝገብ ሹም ፊት በመቅረብ ፈቃዳቸውን ሲገልጹና የክብር መዝገብ ሹሙም ይህንኑ ፈቃዳቸውን ሲቀበል ይፈጸማል።

ይሁን እንጂ ይህ ጋብቻ ፀንቶ ላይቆይ ይችላል። በዚህም ጋብቻው ሲፈርስ የቀድሞ ባለትዳሮቹ ሌላ ጋብቻ ሊመሰርቱ ይችላሉ።

ትዳሯን የፈታች ሴት ሌላ ጋብቻ ለመፈጸም የሚጣልባት ቀነ ገደብ ምን ያህል ነው የሚለውን ርዕሰ ጉዳይ በዛሬው “ሕግ ይዳኘኝ” መርኃ ግብራችን እናያለን።

በቤተሰብ ሕጉ አንቀጽ 16 መሰረት አንዲት ሴት አስቀድሞ የነበራት ጋብቻ ከቀረ በኋላ አንድ መቶ ሰማንያ ቀን ካላለፈ በቀር ሌላ ጋብቻ መፈጸም እንደማትችል ክልከላ ተጥሎባታል፡፡

ነገር ግን ይህ አንድ መቶ ሰማንያ ቀን ሳይደርስ የወለደች እንደሆን ወይም ጋብቻ የምትፈጽመው ከቀድሞ ባሏ ጋር ከሆነ፣ ዕርጉዝ አለመሆኗ በህክምና ከተረጋገጠ ወይም ይህን ጊዜ እንዳትጠብቅ በፍርድ ቤት የተወሰነ እንደሆነ ይህን ጊዜ ሳትጠብቅ ጋብቻ ልትፈጽም እንደምትችል በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 16 (2) ላይ ተቀምጧል፡፡

ይህ ክልከላ በመሰረታዊነት የተቀመጠው የሕፃናትን መብት ለመጠበቅ ነው፡፡ ሕፃናት ወላጆቻቸውን የማወቅና ከወላጆቻቸው እንክብካቤ የማግኘት መብት እንዳላቸው በሕገ መንግስቱ እና በዓለም አቀፍ ስምምነቶች ላይ የተቀመጠ ነው።

በመሆኑም ይህ ክልከላ የሚደረገው የሕፃናትን መብት ለማስከበር እና የወላጆቻቸውለ ማንነት ላይ አከራካሪ ሁኔታ እንዳይፈጠር ነው፡፡

በብርሃኑ አበራ