ጥቅምት 13/2017 (አዲስ ዋልታ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአፍሪካ ሀገራት ዋንጫ (ቻን) ማጣርያ የሚያደርጋቸው ጨዋታዎችን በአሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ጊዜያዊ ዋና አሰልጣኝነት እየተመራ እንዲያከናውን መወሰኑን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታወቀ፡፡
አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ላለፉት 12 ወራት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ምክትል አሰልጣኝ ሆነው ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከኤርትራ ጋር የሚያከናውናቸውን ጨዋታዎች ጨምሮ የቻን ማጣርያን በጊዜያዊ ዋና አሰልጣኝነት የሚመሩ መሆኑን ከፌዴሬሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
መሳይ ተፈሪ በክለብ ደረጃ ወላይታ ድቻን ከምስረታው ጀምሮ በፕሪምየር ሊግ ተሳታፊ እንዲሆንና በ8 ዓመት ቆይታው በ2009 የኢትዮጵያ ዋንጫን በማሳካት በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ እንዲሳተፍ አስችሏል፡፡
አርባ ምንጭ ከተማን በዋና አሰልጣኝነት በመምራት በ2015 ዳግም ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ እንዲመለስም አድርጓል፡