ሩሲያ ከሌሎች ሀገራት የምትገዛውን የአበባ ምርት ከኢትዮጵያ ለመግዛት ተስማማች

አዲስ አበባ፣ የካቲት 13፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ከሩሲያ ፌደሬሽን የኢኮኖሚ ልማትና ንግድ ሚኒስትር ማክሲም ሬሸትኒኮቭ ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸውም ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር)÷ ኢትዮጵያና ሩሲያ ዘመናትን የተሻገረ የዲፕሎማሲና የኢኮኖሚ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት መሆናቸው አውስተዋል፡፡

ነባሩን ታሪካዊ ግንኙነት መሰረት በማድረግ በሀገራቱ መካከል ጠንካራ የንግድ ትብብር መፍጠር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ምክክር መደረጉንም ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያን ወጪ ንግድ በሩሲያ ለማስፋፋት ስምምነት ላይ መደረሱን የገለጹት ሚኒስትሩ÷በተለይም ሩሲያ ከሌሎች ሀገራት የምትገዛውን የአበባ ምርት ከኢትዮጵያ እንድታስገባ መስማማታቸውን በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው አስፍረዋል፡፡

ማክሲም ሬሸትኒኮቭ በበኩላቸው÷ኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ድርጅት አባል ለመሆን የምታደርገውን ጥረት እንደሚያግዙ ቃል ገብተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከኢኮኖሚ ማሻሻያው ወዲህ በተለያዩ ዘርፎች እያሳየች ያለው ኢኮኖሚያዊ ለውጥ የሚበረታታ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

የሁለቱ ሀገራት የንግድ ግንኙነት እያደገ መምጣቱን ጠቁመው÷በፈረንጆቹ 2024 ብቻ ኢትዮጵያና ሩሲያ 389 ሚሊየን ዶላር የሚደርስ የንግድ ግብይት መፈጸማቸውን አመላክተዋል፡፡