የሰው ሰራሽ አስተውሎት ተመራማሪዎችን በተለያዩ ሳይንሳዊ ምርምሮች ላይ እያገዘ ቢሆንም ራሱን ችሎ ሳይንሳዊ ምርምር ለማድረግ እና አዲስ እውቀትን ለመፍጠር ውስንነቶች ይታያሉ።
ቶኪዮ የሚገኘው ሳካና ሰው ሰራሽ አስተውሎት የተባለው ተቋም በዓለማችን ላይ የመጀመሪያ የሆነውን ሰው ሰራሽ አስተውሎት (ኤ.አይ) ሳይንቲስትን ሮቦት ሰርቷል።
የሰው ሰራሽ አስተውሎት ምርምር እና ልማት ተቋም በሰው ሰራሽ አስተውሎት የሚንቀሳቀስ እና ማሽን ማስተማር የሚችል አዳዲስ ሳይንሳዊ ግኝቶችን መስራት የሚችል ሞዴል አስተዋውቋል፡፡
ሰው ሰራሽ አስተውሎት ሳይንቲስቱ ጄኔሬቲቭ ኤ.አይ ሞዴል የሚል ስያሜ የተሰጠው ሲሆን አጠቃላይ የጥናት እና ምርምር ሥርዓቱን ራስመር (አውቶማቲክ) በሆነ መንገድ ያዘጋጃል፡፡
በዚህም ሞዴሉ በሚሰራው ስራ አዳዲስ ሀሳቦችን ማመንጨት፣ ምርምሩ የሚዘጋጅበትን ስልት መንደፍ፣ ሙከራዎችን ማድረግ እና ግኝቶቹን በሳይንሳዊ ጽሁፎች ማቅረብን ያካትታል፡፡
በተጨማሪም ይህ ሥርዓት የምርምር ወረቀቶችን የሰው ልጆች በሚገመግሙበት ደረጃ የመመልከትና ግብረ መልስ የመጻፍ ተጨማሪ አቅሞች አሉት ተብሏል።
ሥርዓቱ በዋናነት ለተቋማዊ እና በጥናት ላይ ላተኮሩ ተግባራት አገልግሎት እንዲሰጥ ታስቦ የተሰራ ሞዴል ነው፡፡
ሞዴሉ ከፍተኛ የመፈጸም አቅም ያላቸውን ኮምፒዩተሮች ለአገልግሎቱ እንደሚጠቀም የሳካና ኤ.አይ ድረ-ገጽ አስነብቧል።
በየኔወርቅ መኮንን