ቀፎው ተነክቷል!

(በነስረዲን ኑሩ )

የቀዳሚና ገናና ታሪክ ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ፣ ሚሊየን ጀግኖችን የወለድችው ኢትዮጵያ ዛሬ ተደፍራለች።

ከሶስት ሺህ ዘመናት በላይ ባስቆጠረው ታሪኳ የውጭ ጠላቶችን አጥታ እንደማታውቅ ሁሉ፤ ከማህፀኗ ተፈጥረው መልሰው የሚወጓት የክብሪት ፍሬዎችም ሞልተዋታል።

አብዲሳ አጋን፣ በላይ ዘለቀን፣ አሉላ አባነጋን፣ ዑመር ሰመተርን እና መሰል ጀግኖችን አምጦ በወለደው አንጀቷ፤ ሆድ አደር እና ተላላኪ ባንዳዎችንም አፍርታለች።

እነዚህ ባንዳና የናት ጡት ነካሾች፤ የኢትዮ ጣሊያንን ጦርነት ጨምሮ ኢትዮጵያ ችግር ውስጥ በገባችባቸው ወቅቶች ከውጭ ጠላት ጋር አብረው እንደወጓት ታሪክ ይነግረናል።

የውጭ ወራሪዎቿና የውስጥ ወርዋሪዎቿ ይፈትኗት ቢሆን እንጂ፤ እቅዳቸው ሰምሮ አንበርክከዋት አያውቁም። ምክንያቱም ኢትዮጵያዊያን ለመንበርከክ አልተፈጠሩምና።

ኢትዮጵያን አሁን የገጠማት ፈተና ግን የተደራጀና የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች በአንድ ላይ የተሰለፉበት ነው። ለዚህ ደግሞ ማርከሻው ውስጣዊ ልዩነቶች ቢኖሩ እንኳን ልዩነቶቹን በይደር አቆይቶ ፈተናውን ለመመከት በአንድነት መቆም ነው።

ላለፉት ሶስት አስርት አመታት ኢትዮጵያን ሲያደማ እና ኢትዮጵያዊነትን ሲያዋርድ የነበረው አሸባሪው የህወሃት ቡድን ደግሞ ኢትዮጵያን ለማጥፋት የተጠነሰሰውን ሴራ ከማዘጋጀት አንስቶ ወደ ተግባር እስከመቀየር ድረስ ዋነኛው ተዋናይ ነው።

በህዝብ እምቢተኝነት ከሶስት አመታት በፊት በኢትዮጵያ እና በዜጎቿ እጣ ፈንታ ላይ አዛዥ ከነበረበት ስልጣን ተገዶ እንዲወርድ ከተደረገበት ማግስት አንስቶ መቀሌ በመመሸግ ከታሪካዊ ጠላቶቻችን ጋር ግንባር በመፍጠር ኢትዮጵያን የማጥፋት እንቅስቃሴ ውስጥ መግባቱ ይታወቃል።

የሃሰተኛ መረጃዎች ወላጅ አባት የሆነው ይህ አሸባሪ ቡድን መቀሌ እንደመሸገ የመጀመሪያ ተግባሩ ያደረገው  በክልሉ በሚገኙ መገናኛ ብዙሃን ሁሉ ሀሰተኛ መረጃዎችን ሲያሰራጭ ውሎ ማደር እንደነበር የኢትዮጵያ ህዝብ የሚያስታውሰው ሀቅ ነው።

ከዚህም ባሻገር ከደሃው የኢትዮጵያ ህዝብ ጉሮሮ ነጥቆ ያከማቸውን ከፍተኛ ገንዘብ በመጠቀም ከ20 ሺህ በላይ አባላት እንዳሉት የተነገረለት “ዲጂታል ወያኔ” የተሰኘ የሃሰተኛ መረጃዎች መፈልፈያ፣ ማሳደጊያ እና ማሰራጫ የሚዲያ ሰራዊት ገነባ።

የዚህ የሃሰተኛ መረጃ ሰራዊት ዋነኛ ተግባር ሀሰተኛ መረጃዎችን የሰራዊቱ አባላት በሆኑ ከ20 ሺህ በላይ የፌስ ቡክ ገፆች ላይ በማስተጋባት እውነት እንዲመስል ማድረግ ነው።

አሸባሪው ቡድን በዚህ ብቻ ሳይገደብ በዓለም አቀፍ የሚዲያ ተቋማት ውስጥ የሚሰሩ ጋዜጠኞችን እና የሎቢ ቡድኖችን በከፍተኛ ገንዘብ በመግዛት ኢትዮጵያዊያንን ግራ የሚያጋቡ ሃሰተኛ መረጃ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተለያዩ ቋንቋዎች እንዲነገርለትና ዓለም የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲይዝ ከፍተኛ ስራ ሰርቷል።

በዚህ ተግባሩ አሜሪካን ጨምሮ በርካታ ሃገራትን ብሎም ዓለም አቀፍ ተቋማትን ማሳሳትና ከጎኑ ማሰለፍ የቻለ ቢሆንም የኢትዮጵያ ህዝብን ሊያሳስት ግን አልተቻለውም።

የኢትዮጵያ ህዝብ ምንም እንኳ የአሸባሪ ቡድኑን የ27 አመታት ግፍ በይቅርታ ያለፈው ቢሆንም የሰሜን እዝን ከጀርባው በመውጋት ኢትዮጵያን የመበታተን ተግባሩን ሲጀምር ግን ይቅር ሊለው የማይችለው ጉዳይ ሆኖበታል።

ሆደ ሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ፣ ቅድሚያን ለዲፕሎማሲ የሚሰጥ ቢሆንም  ኢትዮጵያ ስትነካበት ይቆጣል።

ዛሬ በመቃብሩ አፋፍ ላይ ባለው  ሽብርተኛ ቡድን እና አንዳንድ የውጭ ሃገራት በኢትዮጵያ ላይ የተቃጣው ጥቃትና ሉአላዊነትን የመዳፈር አካሄድ ህዝቡን በእጅጉ አስቆጥቷል።

የእናት ሃገሩን መደፈር በትዕግስት ሊያልፈው የማይችለው ሆነበትና እነሆ የኢትዮጵያ ጠላቶችን ወደ ሲኦል ለመላክ በአንድነት እና በተጠንቀቅ ቆሟል።

መላው ኢትዮጵያዊ የተለያዩ ድጋፎችን ከማድረግ አንስቶ የሃገር መከላከያ ሰራዊትን ተቀላቅሎ በግንባር እስከ መፋለም የሚደርስ ንቅናቄ ውስጥ ገብቷል።

ይህ ጀግና ህዝብ፤ ድንበራችንን ጥሶ እስከ 700 ኪሎ ሜትር ወደ ሃገራችን ዘልቆ የገባውን የዚያድ ባሬን ሰራዊት በፍፁም ኢትዮጵያዊ የሃገር ፍቅር፣ ወኔና ጀግንነት ረግጦ፣ ሰብሮና ጠራርጎ ያስወጣ ህዝብ ነው።

ይህ ትውልድም የ1969ኙን ታሪክ በመድገም ኢትዮጵያን ከጠላቶቿ መንጋጋ ለመንጠቅ ተዘጋጅቷል።

የቃል ኪዳኗን ሃገር ይመኟታል እንጂ አይበሏትም። ቀፎው ሲነካ ህዝቡ ቀፎውን ነቅቶ ይጠብቃልና።