ሚያዚያ 15 /2013 (ዋልታ) – የቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ቡድን ጌታነህ ከበደን፣ አስቻለው ታመነ፣ ጋዲሳ መብራቴንና ሙሉዓለም መስፍንን ከዋናው የእግር ኳስ ቡድን ማገዱን አስታወቀ።
የቅዱስ ጊዮርስ ስፖርት ማህበር የአልተጋባ የስነ-ምግባር ችግርና ጥፋት በሚያሳዩ ተጨዋቾቹ ዙሪያ መግለጫ አውጥቷል።
የቅዱስ ጊዮርስ ስፖርት ማህበር ለእግርኳስ ቡድኑ ውጤት መምጣት ሰፊ ስራዎችን እያከናወነ በሚገኝብተት በዚህ ወቅት ቡድኑ እየተደረገለት ካለው ሁሉን አቀፍ ድጋፍ አንጻር የሚጠበቅበትን ያህል አርኪ የሚባል እንቅስቃሴዎችን እያደረገ አለመሆኑ ይታወቃል ብሏል፡፡
“በዚህ ሁኔታ ውስጥ ባለንበት ጊዜ ደግሞ አልፎ አልፎ በቡድኑ ውስጥ ያሉ አንዳንድ ተጫዋቾቻችን የሚያሳዩት ያልተገባ ባህሪና የስነ-ምግባር ጉድለት እጅጉን የሚያስቆጭ ነው” ሲል ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።
ትናንት ቡድኑን በድሬዳዋ ስታዲየም ከጅማ አባጅፋር ጋር ካካሄደው ከ20ኛ ሳምንት ጨዋታ በኃላ ጌታነህ ከበደ፣ አስቻለው ታመነ፣ ጋዲሳ መብራቴ እና ሙሉዓለም መስፍን ከፍተኛ የዲሲፒሊን ግድፈት መፈጸማቸውን ገልጿል።
ከዚህ ቀደም አብዛኞቹ ተጫዋቾች ቡድኑ በባህርዳር በነበረው ቆይታም የስነ ምግባር ጉድለት ፈጽመው የነበረ ቢሆንም አጠቃላይ ለቡድኑ ውጤታማነትና አንድነት ሲባል በማስጠንቀቂያ እንዲታለፉ ተደርጎ እንደነበርም አስታውሷል።
የክለቡ ስራ አመራር ቦርድ ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ ተጫዋቾቹ በፈጸሟቸው የዲስፕሊን ግድፈቶች ዙሪያ የቡድን መሪው በሚያቀርቡት ሪፖርት ላይ ቦርዱ ውሳኔ እስከሚሰጥ ድረስ ለጊዜው ከቡድኑ ታግደው እንዲቆዩ ተወስኗል ብሏል፡፡
ስለሆነም አራቱም ተጫዋቾች ከድሬዳዋ በዛሬው እለት ወደ አዲስ አበባ እንዲመለሱ መደረጉን የኢዜአ ዘገባ ያመላክታል፡፡