በባሌና ሮቤ ከተሞች እየተገነቡ የሚገኙ ፕሮጀክቶች ምልከታ ተደረገ

በአቶ አዲሱ አረጋ የተመራ ልዑክ

በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ አቶ አዲሱ አረጋ የተመራ የክልሉ ልዑክ በባሌና ሮቤ ከተሞች ከአንድ ዓመት እስከ ሁለት ወር ባሉት ጊዜያት ውስጥ የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን ጎብኝተዋል።

በከተሞቹ እየተገነቡ ከሚገኙ ከ60 ያላነሱ ፕሮጀክቶች መካከል የሮቤ ዘመናዊ የአውቶቡስ ተርሚናል፣ የእናቶች እና ህፃናት ሆስፒታል፣ የአግሮ ኢንዱስትሪ፣ የፓርክ እና ኢፋ ቦሩ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሚጠቀሱ ናቸው።

ከ220 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተመደበለት የሮቤ ዘመናዊ የአውቶቡስ ተርሚናል ለአጎራባች ከተሞች እና ክልሎች በማዕከልነት የሚያገለግል እንደሆነ ነው የተገለፀው።

ተርሚናሉ በውስጡ ዘመናዊ የደህንነት መፈተሻዎች፣ የህክምና ማዕከል፣ ጋራዥ እና የአሽከርካሪዎች ማረፊያ ያሉት መሆኑ ተገልጿል፡፡

በአንድ ጊዜ ከ160 በላይ አውቶቡሶችን ማስተናገድ የሚችለው ተርሚናሉ በሚቀጥሉት ሁለት ወራት ግንባታው ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።

በተያያዘም ከ700 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የሚጠይቀው የግብርና ግብዓቶች ማዘጋጃ ኢንዱስትሪ ፓርክ እና የክልሉ መንግስት በበጀት አመቱ በኢፋ ቦሩ ፕሮጀክት ሊገነባቸው ካቀደቸው አንድ መቶ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ አንዱ እና በ40 ሚሊየን ብር እየተገነባ ያለው ትምህርት ቤት ተጎብኝቷል።

በግንባታ ላይ ያለው የኢንዱስትሪ ፓርክ አካባቢው በግብርና ግብዓቶች የበለፀገ በመሆኑ ጥቅሙ የጎላ እንደሆነ አቶ አዲሱ አረጋ ተናግረዋል።

ኢፋ ቦሩ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትን ጨምሮ የመዋዕለ ህፃናት፣ የመንገድና የመጠጥ ውሃ ግንባታ እንዲሁም ሆስፒታሎች በተቀመጠላቸው የጊዜ እና የጥራት ደረጃ እየተከናወኑ እንደሚገኝ ነው አቶ አዲሱ የገለፁት።

ፕሮጀክቶቹ ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል ከመፍጠራቸውም በላይ ህብረተሰቡ ሲያነሳቸው ለነበሩ ጥያቄዎች መልስ የሚሆን እና መንግስት የገባቸውን ቃል የሚፈፅም ለመሆናቸው ማሳያዎች ናቸው ብለዋል አቶ አዲሱ።

ፕሮጀክቶቹ የሚገኙት ህዝብ ጥያቄ ስላነሳባቸው ብቻ ሳይሆን ልማቱ ለአከባቢው አስፈላጊ መሆኑም አቶ አዲሱ አረጋ በተለይም ከዋልታ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል።

የአካባቢው ነዋሪዎች እየተካሄዱ ባሉ የልማት ስራዎች ደስተኞች መሆናቸውን ገልጸው ከመንግስት ጎን እንደሚቆሙም ተናግረዋል።

(በሚልኪያስ አዱኛ)