በቤኒሻንጉል ጉሙዝ የፖሊዮ ክትባት ከነገ ጀምሮ እስከ መጋቢት 20 እንደሚሰጥ ተገለጸ

አቶ ፈቃዱ ረጋሳ

መጋቢት 16/2013 (ዋልታ) – በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ዕድሜያቸው ከ5 ዓመት በታች ለሆኑ ህጻናት የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ ከነገ ጀምሮ እስከ መጋቢት 20 እንደሚካሄድ የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ፡፡

የቢሮው ኃላፊ አቶ ፈቃዱ ረጋሳ ዘመቻውን አስመልክተው እንደገለጹት፣ የክትባት ዘመቻው ከመተከል ዞን ውጪ በሚገኙ የክልሉ ሁሉም አካባቢዎች ይካሄዳል፡፡

ቤት ለቤት በሚሰጠው የፖሊዮ ክትባት 124 ሺህ 497 ህጻናት እንደሚከተቡ የሚጠበቅ ሲሆን፣ ክትባቱ ቤት ለቤት የሚሰጥ በመሆኑ በመተከል ዞን ካለው ወቅታዊ ሁኔታ አኳያ በዞኑ ዘመቻውን ማካሄድ እንዳልተቻለ አቶ ፈቃዱ ተናግረዋል፡፡ በዞኑ በቀጣይ ክትባቱን መስጠት የሚያስችል ሁኔታ ሲፈጠር ዘመቻው ይካሄዳልም ነው ያሉት፡፡

የቅድመ ዝግጅት ሥራ ማጠናቀቁን የጠቆሙት ኃላፊው፣ ከአጋር አካላት ጋር በመሆን ክትባቱ በሚሰጥባቸው አካባቢዎች አስፈላጊ ቁሳቁስ ቀድመው መድረሳቸውን ገልጸዋል፡፡

ለክትባት ዘመቻው መሳካት አመራሩ፣ ወላጆች፣ ከ5 ዓመት በታች የሆኑ ህጻናት ማቆያ ትምህርት ቤቶችና መላው ህብረተሰብ የበኩላቸውን ትብብር እንዲያደርጉ አቶ ፈቃዱ ጥሪ ማቅረባቸውን ከክልሉ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጽህፍት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡