በቴክኖሎጂ የተደገፉ ሴቶች ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች መስፋፋታቸውን አንድ ጥናት አመለከተ

ግንቦት 1/2016 (አዲስ ዋልታ) የጥላቻ ንግግርን ጨምሮ በቴክኖሎጂ የተደገፉ ሴቶች ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች መስፋፋታቸውን ሴንተር ፎር ኢንፎርሜሽን ሪዚሊየንስ (CIR) የተሰኝ ተቋም ያስጠናው ጥናት አመላከተ።

በጥናቱ ኢትዮጵያ ውስጥ ሴቶች በተለያዩ ማህበራዊ ትሥሥር ድረ-ገፆች በሚደርስባቸው ጥቃት እና ትንኮሳዎች ሳቢያ ማሀበራዊ መስተጋብሮቻቸው ሙሉ እና ትርጉም ያለው ተሳትፎ እንዳያደርጉ እንቅፋት መሆኑን ጠቁሟል።

ጥናቱ በሁሉም የማህበራዊ የትስስር ገጾች ላይ እንደሚስተዋሉ የገለጸ ሲሆን ችግሩ በተለይ በፌስቡክ ላይ አይሎ መታየቱ ጥናቱ ያሳያል።

ጥናቱ ጨምሮም በሴቶች ላይ በማህበራዊ የትስስር ገጾች የሚቃጡ ጥቃቶች እየተለመዱ እንደመጡ እና የስርዓተ-ፆታ ይዘት ያላቸው ጥቃቶች እንደመደበኛ ነገር እያታዩ እንደመጡ አመላክቷል።

ጥናቱ በሁለት ክገፍሎች የተከናወነ ሲሆን የመጀመሪያው ክፍል በኢትዮጵያ በመገናኛ ብዙሃን፣ በሲቪል ማህበራት እና በሲቪል ሰርቪስ ውስጥ ቁልፍ ሚና ያላቸውን እና ለኦንላይን ጥቃቶች ተጋላጭ ከነበሩ 14 ሴቶች ጋር ቃለ-ምልልስ በማድረግ የተሰራ ነው።

ሁለተኛው ክፍል በኤክስ (የቀድሞው ትዊተር)፣ ቴሌግራም እና ፌስቡክ በአራት ቋንቋዎች በአማርኛ፣ በአፋን ኦሮሞ፣ በትግርኛ እና በእንግሊዘኛ የተጋሩ የማህበራዊ ሚዲያ ይዘቶችን በመተንተን እንደተጠና ተገልጿል።

በውጤቱም ሁለቱም ጾታዎች በማህበራዊ የትስስር ገጾች አማካኝነት በሚሰነዘሩ ጥቃቶችና የጥላቻ ንግግሮች ተጋላጭ ቢሆኑም ችግሩ በሴቶች ላይ ገዝፎ መታየቱን ነው የተጠቀሰው። ከዚህ ባለፈም ጥቃቶቹ በባህርይ፣ በዓላማና ተፅዕኖ በሁለቱ ጾታዎች ላይ ልዩነት እንዳለ ተመላክቷል።

በዚህ መሰረትም በወንዶች ላይ የሚደርሰው ጥቃት በወንዶች የፖለቲካ አመለካከት ላይ ሲያተኩር በሴቶች ላይ ግን መልካቸውን፣ የጋባቻ ሁኔታን፣ ስርዓት ጾታን፣ የጾታ ሚናን እና ማንነታቸውን የሚያንኳስሱ ይዘቶች እንዳላቸው ጥናቱ ያሳያል።

በዚህም ተጠቂዎቹ ስማቸው እንደጎደ፣ ለስነ ልቦናዊ ጉዳት እንደተዳረጉና በስራ፣ በግልና በቤተሰቦቻቸው ህይወት ላይ ተፅዕኖ እንዳሳደረባቸው ገልፀዋል።

እነዚህ የተንሰራፉ የስርዓተ-ፆታ መሰረት ያደረጉ የጥላቻ ንግግሮች ብዙውን ጊዜ ከማስፈራሪያ ወይም ከአደገኛ ንግግሮች ያነሰ ጉዳት እንዳላቸው ቢታሰብም የጥላቻ ንግግሮች የሴቶችን የማህበራዊ ሕይወት ውስጥ ያላቸውን ተሳትፎ እንዲቀንስ በማድረግ ዘላቂ ማኅበረሰባዊ ተጽእኖ ሊኖራቸው እንደሚችል ተመላክቷል።