በቶኪዮ ኦሎምፒክ በአትሌቲክስ ስምንት ሜዳሊያዎችን ለማግኘት ታቅዷል

በቶኪዮ ኦሎምፒክ በአትሌቲክስ ውድድር ስምንት ሜዳሊያዎችን ለማግኘት ማቀዱን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አስታወቀ።

የኢትዮጵያ አትሌትክስ ፌዴሬሽን 24ኛ ጠቅላላ መደበኛ ጉባኤውን አካሂዷል።

የፌዴሬሽኑ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ቢልልኝ መቆያ በጉባኤው ላይ እንደገለጹት፣ በዚህ ዓመት በሚካሄደው የቶኪዮ ኦሊምፒክ 36 አትሌቶችን በአትሌቲክስ ስፖርት ለማሳተፍ ታቅዷል።

በዚህ የኦሎምፒክ ስፖርት ከሚሳተፉ አትሌቶች 2 ወርቅ፣ 2 ብርና 4 የነሐስ ሜዳሊያ ለማግኘት መታቀዱንም ነው የገለጹት።

አሁን ላይ ከ100 በላይ አትሌቶች ተመርጠው ለውድድሩ በዝግጅት ላይ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

ከእነዚህ አትሌቶች መካከል የተሻለ ብቃት ያላቸው 36 አትሌቶች ተመርጠው የውድድሩ ተሳታፊ ይሆናሉ መባሉን ኢዜአ ዘግቧል።