በእብሪት የምንወርበት ምክንያት አይኑረን እንጂ የምንሞትላት አገር አለችን!

በእብሪት የምንወርበት ምክንያት አይኑረን እንጂ የምንሞትላት አገር አለችን!

በነስረዲን ኑሩ

ጥቅምት 28/2014 (ዋልታ) ኢትዮጵያን ከተቻለ በዘመናዊ ቅኝ ገዢነት ማስተዳደር ካልሆነ ደግሞ የማፈራረስ ዓላማን አንግበው የተነሱት ጠላቶቻችን የሚይዙት የሚጨብጡት ጠፍቷቸዋል።

ግን ደግሞ ውሸትን በመደጋጋም እውነት ሊያስመስሉትና በገንዘብ መጠናቸው ልክ ሊያስፈራሩን ይሞክራሉ፤ ዳሩ ግን ኢትዮጵያዊያን በአገር ክብርና ነፃነት ጉዳይ ወይ ፍንክች ማለት የአያት ቅድመ አያታችን ነው፡፡

የውጭ ጠላቶቻችን ለእኩይ ዓላማቸው ስኬት እንደሚያግዛቸው በብዙ ተስፋ የጣሉበት፣ በሰብኣዊ ድጋፍ ስም ትጥቅና ስንቅ ያቀበሉት እና በአንቀልባ እንደሚታዘል ጨቅላ አልሚ ምግብ ያጎረሱት አሸባሪው ትሕነግ የተሰጠውን አገር የማፍረስ የቤት ሥራ በፈለጉት ልክ እየተወጣላቸው እንዳልሆነ ተረድተውታል።

በዚህም በተለይ አሜሪካ በሰብኣዊ ድጋፍ ምስል የተለበጠ ጭምብሏን አውልቃ ለመጣልና እርቃኗን ብቅ ለማለት ተገዳለች። የምጣኔ ሃብት ማበረታቻው አግዋ ለግልፅ የፖለቲካ ፍጆታ ሲውል ከሰሞኑ አይተናል፡፡ ሆኖም እኛ በአግዋ የተፈጠርን ሳንሆን እንደ አድዋ ያሉ ታላላቅ ድሎችን የፈጠርንና የጭቁኖች ሁሉ የነፃነት ቀንዲል የሆነን ነን፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ጦርነቱን አስመልክተው ከወራት በፊት በአንድ መድረክ ሲናገሩ “ሕወሓት የሚዋጋው የውክልና ውጊያ ነው” ሲሉ ገልፀው ነበር።

አሸባሪው ትሕነግን ከፊት ለፊት አድርጎ ሲወጋን የነበረው ማን እንደሆነ አሁን ለኢትዮጵያዊያን ብቻ ሳይሆን ለመላው ዓለም ገሃድ ሆኗል። ከሰሞኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ  (ዶ/ር) በወሎ ግንባር የውጭ አገራት ወታደሮች ጭምር መሰለፋቸውን ማሳወቃቸውን እዚህ ላይ ስናክልበት ነገሩ ሁሉ ግልፅ ይሆናል፡፡

ወጊዎቻችን አሜሪካን ጨምሮ በሷ የሚመሩ አንዳንድ ምዕራባዊያን አገራትና ተቋማትም ጭምር ናቸው።

በለፀግን የሚሉት አገራገት የሚጥሉብን ማዕቀቦችን ጨምሮ የሚሰነዘሩብን ዛቻና ማስፈራሪያዎች  ከመንበርከክ ይልቅ ሲያበረታን፣ ከመፍረክረክ ይልቅ አንድ ሲያደርገን ማየታቸው አንገብግቧቸዋል።

ሲኤንኤን፣ ዋንሽንግተን ፖስት፣ ሮይተርስ፣ ዘ ቴሌግራፍ፣ ኒው ዮርክ ታይምስን በመሳሰሉ ልሳኖቻቸው በኢትዮጵያ ላይ የከፈቱት ሃሰተኛ የመረጃ ዘመቻም ቢሆን እንደ ግምባሩ ሁሉ እነሱ እንዳሰቡት ሊሆን አልቻለም።

ተጨንቀውና ተጠበው በፎቶ ሾፕና ተቆራርጠው በተሰፉ ቪዲዮዎች ቅንብር የሚያዘጋጁት ዘጋቢ ፊልም ለእይታ ቀርቦ ብዙም ሳይቆይ በሳተና ኢትዮጵያዊያንና ለእውነቱ በቆሙ ዓለም ዐቀፍ ጋዜጠኞች፣ ፖለቲከኞችና ተንታኞች ሃሰተኝነቱ በማስረጃ ተጋልጦ ሲዋረዱ አይተናል።

አሜሪካስ ብትሆን ኢትዮጵያዊ ሁሉ አገሩ ስትደፈር ቀፎው እንደተነካበት ንብ የሚቆጣ እና ጠላቶቿን አዋርዶና ሰብሮ ሉኣላዊነቷን የሚያስከብር መሆኑን እንዴት ከጣሊያን መማር ተሳናት!?

ዛሬ በአፍሪካ መዲና፣ በዓለም በርካታ ዲፕሎማቶች በሰላም የሚኖሩባት 3ኛዋ የዲፕሎማሲ መናገሻ ከተማ እና የጥቁር እና ጭቁን ሕዝቦች የነፃነት አርማ ኢትዮጵያ መናገሻ በሆነችው አዲስ አበባ ታላቅ የእምቢተኝነት ትዕይንተ ሕዝብ ተካሂዷል።

መላው የመዲናዋ ነዋሪ ኢትዮጵያዊ ወደ ታሪካዊው የመስቀል አደባባይ በመትመም የቅኝ ግዛት አስተሳሰብ እንደሚፀየፍ እና እሱን የሚሸከም ትከሻ እንደሌለው ለመላው ዓለም በድጋሚ አረጋግጧል።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚህ ወቅት ባስተላለፉት ትውልድ ተሻጋሪ መልእክታቸው የአድዋ ልጆችን በአግዋ ማስፈራራት እንደማይቻል ለጠላቶቻችን በግልጽ ቋንቋ ነግረዋቸዋል።

አሜሪካ እንደ አጋሯ ትሕነግ ሁሉ ከ50 ዓመታት በፊት በተቀበረው የቅኝ ገዢነት አባዜ ውስጥ ተዘፍቃ ያልበላትን ስታክና የሰው ስታቦካ የራሷ እያረረባት ለመሆኑ የቻይና፣ ሩሲያ እና ቱርክ አሁናዊ ሁኔታ በቂ ማሳያ ነው።

ቻይና፣ ራሲያ እና ቱርክ እጅግ ዘመናዊ አውዳሚ የጦር መሳሪያዎችን በማምረት እና በመታጠቅ፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ በመራቀቅ እና ምጣኔሃብታቸውን በማይታመን ፍጥነት በማሳደግ ለእብሪተኛዋና ቀዳሚዋ እኔ ብቻ ነኝ  በሚል ለምትታበየው አገር አሜሪካ የቀን ቅዠት ከሆኑ ቆይተዋል።

የማደግ ተስፋን ሰንቀው በተጨባጭ የእድገት መንገድ ላይ ባሉ አዳጊ አገራት የውስጥ ጉዳይ ገብታ እና ከአንድ የአሸባሪ ቡድን ጋር የማይዘልቅ ጋብቻ ፈፅማ ከምትርመጠመጥ በእነ ቻይና የተወሰደባትን የበላይነት ባትመልስ እንኳን ልዩነቱ እንዳይሰፋ ብትተጋ ይሻላት ነበር።

የዓለም ሚዛን እየተቀየረ ባለበት በዚህ ወቅት መገናኛ ብዙኃናቸው አንድ ሐሙስ የቀረውን እና ሞቱ እርግጥ የሆነውን አሸባሪ ቡድን ለማዳን ሃሰተኛ መረጃን በማዘጋጀትና ማሰራጨት የሽብር ቡድኑን በሐሰብ አዲስ አበባ አስገብተው ሲያስቦርቁት ማየት ያሳፍራል። ዳሩ ግን መመኘት ይቻላል፤ ማድረጉ አይሳካም እንጂ፡፡ ያገሬ ሰው ለአፍ መንገድ የለው ይላል! ሰው እንደፈለገው ያውራ ሲል ነው፡፡

እነሱ ደከሙ እነሱ ቀለሉ እንጂ ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት ኢራቅን፣ አፍጋኒስታንን፣ ሊቢያን እና ሶሪያን ለማፈራረስ የተጠቀመችበትን ተመሳሳይ ቀመር ኢትዮጵያ ላይ እንዲሰራ መድከም ትርፉ ጉንጭ ማልፋት ነው፤ ምክንያቱ ደግሞ ይህቺ አገር ሶሪያ አሊያም ሊቢያ ሳትሆን ኢትዮጵያ ነች።

ኢትዮጵያዊን በፍቅር ትረታዋለህ፤ ቤቱ በእንግድነት ሄደህ አልጋውን ለቆልህ መሬት ላይ ቢተኛ ኩራት ቢሰማው እንጂ አይቆረቁረውም። ነገር ግን ታመህም ይሁን ተጣመህ በአገሩ ከመጣህ ይቆረቁረዋል፤ ያመዋል፤ ይከነክነዋል፤ ያንገበግበዋል።

በእንዲህ ሁኔታ ቁጣው ገንፍሎ ከተነሳ እናት አገሩን የደፈረበትን ወንበዴ እና ያስደፈረበትን ባንዳ ሳይቀብር አይቀመጥም። ኻላስ!

ዚያድ ባሬ በኢትዮጵያ ሉኣላዊ ግዛት ውስጥ በመስፋፋት ታላቋን ሶማሊያ እመሰርታለሁ ብሎ በእብሪትና ማን አህሎኝነት ስሜት በመነሳሳት በምስራቁ የኢትዮጵያ ክፍል ድንገት ወረራ በመፈጸም እስከ 700 ኪሎ ሜትሮች ድረስ ዘልቆ መቆጣጠር ችሎ ነበር።

ዚያድ ባሬ ወረራውን እንፈጽም ሁለት ምክንያቶች ነበሩት፤ በወቅቱ ኢትዮጵያ በውስጥ ሹቻና እዚህም እዚያም በሚፈነዱ ውጊያዎች ተዳክማለች ብሎ ማሰቡና ታሪካዊ ጠላቶቻችን እስከአፍንጫው ያስታጠቁት ዘመናዊ የጦር መሳሪያ ድልን ያመጣልኛል ብሎ ማመኑ ናቸው።

በዚህም ዚያድ ባሬ የሚዋጋው እና ድል የሚያመጣው መሳሪያ ሳይሆን ልብ መሆኑን፤ ወራሪ እና ተወራሪ በዳይና ተበዳይ የሚዋጉበት ስነ ልቦና እና ወኔ እንደሚለያይ እና በዋናነት ኢትዮጵያን ማፍረስና ማዋረድ የማይቻል ከመሆኑም ባሻገር ዋጋ የሚያስከፍል መሆኑን ከጣሊያን አለመማሩን ማየት ይቻላል።

በውጤቱም ተዳክማለች ተብላ የታሰበችው ኢትዮጵያ ያስተላለፈችውን የክተት አዋጅ ተቀብሎ የተመመው አርሶ አደር ዘመኑ ያፈራቸውን የጦር መሳሪያ የታጠቀውንና በቂ ወታደራዊ ሥልጠና ያገኘውን ወራሪ ሰራዊት ሰብሮ፣ ረግጦና ጠራርገጎ ከሉኣላዊ ግዛቱ እንዲያስወጣው ሆኗል።

ኢትዮጵያ በታሪኳ የማንንም ድንበር ጥሳ፣ ወረራ ፈፅማና ንፁሃን ገድላ አታውቅም፤ የምንወርበት እና የምንገልበት ምክንያት የለንምና።

በደምና አጥንታችን የምናፀናትና የምንሞትላት አገር ግን አለችን – ኢትዮጵያ!