በፕሪሚየር ሊጉ ባህርዳር ከተማ አዳማ ከተማን 1 ለ 0 አሸነፈ

መጋቢት 01/2013 (ዋልታ) – በቤት ኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ16ኛ ሳምንት ጨዋታ ባህር ዳር ከተማ ድል ሲቀናው ወላይታ ዲቻ ነጥብ ተጋርቷል፡፡

የፕሪምየር ሊጉ የባህር ዳር የመጨረሻ ጨዋታዎች ዛሬ መከናወን ሲጀምሩ ከሰዓት በኋላ በተደረገ ጨዋታ ባህር ዳር ከተማ አዳማ ከተማን አሸንፏል፡፡

በፍፁም አለሙ አማካኝነት በተቆጠረች ብቸኛ ግብ ያሸነፉት የጣና ሞገዶቹ ነጥባቸውን 26 በማድረስ በፕሪምየር ሉጉ የደረጃ ሰንጠረዥ 3ኛ ደረጀ ላይ መቀመጥም ችለዋል፡፡

ባህር ዳር ከተማዎች በ2ኛ ዙር የቤት ኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የባህር ዳር ቆይታ ከ5 ጨዋታ በ2 አቻ ተለያይው በ3 ጨዋታዎች ድል አድርገዋል፡፡

በአንፃሩ አዳማ ከተማዎች በ5 ጨዋታዎች ሽንፈት አስተናግደዋል፡፡

ረፋድ 4 ሰዓት ላይ በተደረገ ጨዋታ ወላይታ ዲቻ እና ወልቂጤ ከተማ አንድ አቻ ተለያይዋል፡፡

በጨዋታው ወላይታ ዲቻዎች በስንታየሁ መንግስቱ በተቆጠረች ግብ ቀዳሚ ቢሆኑም አህመድ ሁሴን ወልቂጤ ከተማን አቻ ያደረገች ግብ አስቆጥሮ ጨዋታው በአቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡

የቤት ኪንግ የኢትጵያ ፕሪምየር ሊግ የ16ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ነገም ቀጥው ሲደረጉ ረፋድ 4 ሰዓት ሀዲያ ሆሳዕና ከሲዳማ ቡና በ9 ሰዓት ደግሞ ፋሲል ከነማ ከጅማ አባ ጅፋር ይጫወታሉ፡፡

(በመሰረት ተስፋየ)