ሰኔ 25/2016 (አዲስ ዋልታ) ቢቢሲ ትናንት ፖርቹጋል ከስሎቫኒያ ጋር በነበረ የአውሮፓ ዋንጫ ጥሎ ማለፍ ጨዋታ የፍጹም ቅጣት ምት በሳተው ክርስቲያኖ ሮናልዶ ላይ በጻፈው ሽሙጥ በእግር ኳስ ወዳጆች ተተቸ።
ሮናልዶ ቡድኑ በጭማሪ ሰዓት ያገኘውን የፍጹም ቅጣት ምት ከሳተ በኋል ሲያለቅስ የታዬ ሲሆን ቢቢሲ ሁኔታውን “ሚስቲያኖ ፔናልዶ” በማለት ተጫዋቹ ላይ በመቀለዱ በርካታ የእግር ኳስ ቤተሰብን አስቆጥቷል።
የቀድሞው የቸልሲ ተከላካይ ጆን ቴሪ በኢንስታግራም ገጹ “ልታፍሩ ይገባል” ሲል ቢቢሲን ወርፏል።
ሌላ የእግር ኳስ ታዳሚ ደግሞ የቢቢሲን ተግባር “ርኩስ ድርጊት” ሲለው “ሚስቲያኖ ፔናልዶ የቢቢሲ ጥላቻ ነው” ሲል ገልጾታል።
የቢቢሲ ከሙያዊ ስነምግባር ያፈነገጠ ድርጊት በርካታ የእግር ኳስ አድናቂዎችን ያበሳጨና ያሳዘነ ድርጊት እንደነበር ኢንድፔንደንት ዘግቧል።
በትናንት ምሽቱ ጨዋታ ሮናልዶ የመለያ ምቱን በማስቆጠርና የፖርቱጋል በረኛ ዲያጎ ኮስታ ሶስት የፍጹም ቅጣቶችን በማዳን ቡድኑ ወደ ቀጣዩ ዙር እንዲያልፍ አስችለውታል።