‘ባርነት ወይም ፅኑ ትግል’ የቀረቡልን 2 አማራጮች

በነስረዲን ኑሩ

እናደራድራችሁ የሚሉን አካላት ለኢትዮጵያ ያቀረቡት የድርድር አማራጭ ሰላም ወይም ጦርነት የሚመስለው ካለ እሱ የዋህ አሊያም አውቆ የተኛ ነው።

የቀረቡልን አማራጮች ሁለት ናቸው፤ የአድዋ ጀግኖች ያወረሱንን ነፃነት አሳልፎ በመስጠት የእጅ አዙር ቅኝ ግዛትን መቀበል አሊያም በትግላችን ነፃነታችንን ማስከበር ናቸው፡፡

እውነትና ንጋት እያደር ይጠራል እንዲሉ እንደነ ሲኤንኤን እና ሮይተርስ ድካምና ቅጥፈት ሳይሆን፤ መሬት ላይ ያለውን ሃቅ መሬት ወርደው ጥናት ያደረጉ ተቋማት ይፋ እንዳደረጉት ሆነና እውነት ከኢትዮጵያ ጎን ቆማለች።

በቅርቡ ይፋ የተደረገውና በተባበሩት መንግሥታት የሰብኣዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር እና የኢትዮጵያ ሰብኣዊ መብት ኮሚሽን በጋራ ያደረጉት ጥናት ከሚነሱብን ውንጀላዎች ነፃ ቢያወጡንም ከሳሾቻችን ግን እፍረት ወይም ፀፀት አልተሰማቸውም።

ሪፖርቱ የኢትዮጵያ መንግሥት የዘር ማጥፋት ወንጀል አለመፈፀሙን፣ ፆታዊ ጥቃትንም ሆነ ሰብኣዊ አቅርቦትን (እርዳታ በመከልከል ረሃብን) እንደጦርነት መሳሪያ አልተጠቀመም ሲል ዓመት የዘለቀውን የፅንፈኛ መገናኛ ብዙኃን ዘመቻ ውድቅ ቢያደርገውም ካፈርኩ አይመልሰኝ ሆነና ዛሬም በኢትዮጵያዊያን ላይ በሃሰት መዝመቱን ይዘውታል፡፡

ምክንያቱ ደግሞ ያ ሁሉ ጩኸት፣ ጫጫታና ኹካታ ስለ ሰብኣዊ መብት መከበር አልነበረምና ነው።

ጥናቱ ይፋ ሊደረግ የሰዓታት እድሜ ብቻ ቀርተውት እና ዓለም ውጤቱን እየጠበቀ ባለበት ሁኔታ አሜሪካ ማዕቀብ መጣሏ ብዙ ነገር አመላካችም ነበር።


“እስኪ ከማእቀቡ በፊት የጥናቱን ውጤት ልየው” ሳትል ተጣድፋ ማዕቀብ መጣሏ ላይ ከሰዓታት በኋላ የወጣው ሪፖርት ኢትዮጵያን ነፃ ማውጣቱን ስናይ ምን እየተካሄደብን እንደሆነ ቁልጭ ብሎ ይታየናል።

አሜሪካ በሰብኣዊ መብት ጥሰት ምክንያት ብላ ማዕቀብ ስትጥል ከሰኣታት በኋላ በጅምላ ግድያ (ዘር ማፅዳት) ጭምር የከፋ የሰብኣዊ መብት ጥሰትን እየፈፀመ ያለው የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር አትንኩብኝ የሚለው አሸባሪው ሕወሓት መሆኑ ለዓለም ተገልጧል፡፡

ከሪፖርቱ በኋላ ባሉት ቀናት በኢትዮጵያ እና መንግሥቷ ላይ የሚደረገው ጫና ጋብ ይላል ተብሎ ቢጠበቅም በሚያሳዝን ሁኔታ ዘመቻው መልኩን ቀይሮና ዙሩን አክርሮ ቀጠለ።

ዋና ዋናዎቹ የፅንፈኛ ምዕራባዊያን መገናኛ ብዙኃን በኤዲቶሪያል ቦርዶቻቸው የተቀመጠላቸው የሳምንቱ የትኩረት አቅጣጫ “ኢትዮጵያን የተመለከቱ ዘገባዎችን በብዛትና በሃሰት ማዘጋጀትና ማሰራጨት ነው” የሚል በሚመስል መልኩ የተከፈተብንን ወከባና የምናብ ዓለም ከበባ የምናስታውሰው ነው።

በአምስት የምዕራባዊያን መገናኛ ብዙኃን በ4 ቀናት ብቻ 72 የቅጥፈት ዜናዎች ተፈብርከው መሰራጨታቸው ከላይ ያነሳነውን ሃሳብ ያጠናክርልናል።

በበሬ ወለደ ዘመቻ ዛምቢያ ከአዲስ አበባ ዜጎቿን እንድታስወጣ ባደረገች ሰዓታት ልዩነት የ11 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዶላር ጉርሻን ለዛምቢያ የሰጠችው አሜሪካ ሌላ ተመሳሳይ ድራማ ደግማም ዓለምን አስደምማለች።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል የተሰኘ በሰብኣዊ መብት ዙሪያ የሚሰራ ዓለም ዐቀፍ ድርጅት እቅድ አዘጋጅቶ፣ ጊዜ ሰጥቶ፣ ባለሙያ እና በጀት መድቦ እና በአጠቃላይ የጥናት ደረጃን ባሟላ መልኩ በንፋስ መውጫ የሽብር ቡድኑ ሕወሓት የፈጸመውን አስገድዶ የመድፈር ወንጀል (ፆታዊ ጥቃትን ለጦርነት የማዋል ድርጊት) ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡ ምንም እንኳን የኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ተዘፍቀው ያሉት የውጭዎቹ ፅንፈኛ መገናኛ ብዙኃን ሪፖርቱን በተባለው ልክ መስራት ባይፈልጉም፡፡

አምነስቲ የጥናት ሪፖርቱን ይፋ ሊያደርግ ሰዓታት ሲቀረው በሰብኣዊ መብት ስም የምትነግደው አሜሪካ ሌላ እና ጠንከር ያለ ማዕቀብ መጣሏን አሳወቀች። ማዕቀቡ ማንኛውም አይነት የጦር መሳሪያ (የነብስ ወከፍና የቡድን) ለኢትዮጵያ እንድይሸጥ እግድ የሚጥል ሲሆን ሌሎች አገራትም ይህን እንዲተገብሩ የሚጎተጉት ነው።

እዚህ ላይ አጃኢብ የሚያሰኘው ጉዳይ አሸባሪው ቡድን ውኃ የሚረጭ አሊያም ሎሚ የሚጥልብን ይመስል የጦር መሳሪያ ሽያጭ እገዳው እሱን ያላካተተ መሆኑ ነው።

ጥናቶች ይፋ ሊደረጉ ሰአታት ሲቀራቸው ማአቀብ የሚጣልብን ነገር መደጋገም “አጋጣሚ” ነው ብሎ መውሰድ ይቻል ይሆን?

የሚጠበቀው ሪፖርት ይፋ ሲሆንም የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት በተደጋጋሚ ሲገልፁት እንደነበረው አሸባሪ ቡድኑ በወረረባቸው አካባቢዎች እኩይና ሰይጣናዊ ተግባር መፈፀሙን ያረጋገጠ ነበር።

የአሸባሪው ሕወሓት ታጣቂዎች በአማራ ክልል የነፋስ መውጫ ከተማ ላይ ወረራ በፈጸሙበት ጊዜ ከ70 አስገድዶ መድፈር (የቡድንም ጭምር)፣ ዘረፋ እና አካላዊ ጥቃቶች በተጨማሪ ብሔር ተኮር ስድቦችና ማንቋሸሾች የታጨቁበት ንግግርን ሲናገሩ እንደነበር የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ጥናት አረጋግጧል። ጥናቱ ለናሙናነት በተመረጠው የነፋስ መውጫ ከተማ ላይ መሰራቱን ልብ ስንል የሽብር ቡድኑ በወረራቸውና ገብቶ በወጣባቸው አካባቢዎች ያደረሰው ወድመት ምን ያክል እንደሚሆን መገመት ይቻላል፡፡

አምነስቲ ኢንተርናሽናል ካነጋገራቸው እና በከተማዋ ነዋሪ ከሆኑ 16 ሴቶች መካከል 14ቱ በአሸባሪው ሕወሓት ታጣቂዎች የአስገድዶ መደፈር ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል።

የሆነው ሆኖ ኢትዮጵያ አገራት በራሳቸው ጉዳይ የመወሰን መብት እንዳላቸው የምታውቅ፣ የምታከብርና ለተግባራዊነቱም የምትታገል ሲሆን፤ በፈተናዋ ወቅት ከጎኗ የቆሙትን እና የከዷትን የማታውቅና የምትረሳ ግን አይደለችም።

በምንታወቅበት ጽናት፣ አንድነትና ጀግንነት የተቃጡብንን እና የሚቃጡብንን ጥቃቶች ሁሉ መክተን ኢትዮጵያን እናጸናለን።

በሂደቱም ባርነትን ለመሸከም ያልተፈጠርን ሕዝብ መሆናችንን ለዘነጉ ሁሉ በድጋሚ እናስታውሳቸዋለን።

ለኢትዮጵያዊያን በማንኛውም መመዘኛ ባርነት ምርጫችን ሊሆን እንደማይችልም ነጋሪ አያሻም።