ብሔራዊ የጤና ፍትሃዊነት ስትራቴጂክ ዕቅድ ተዘጋጀ

የጤና ሚኒስቴር በአንደኛው የጤናው ዘርፍ የትራንስፎርሜሽን አጀንዳ የጤና ፍትሃዊነትን ለማረጋገጥ ብሔራዊ የጤና ፍትሃዊነት ስትራቴጂክ ዕቅድ አዘጋጀ፡፡

በአንደኛው የጤናው ዘርፍ የትራንስፎርሜሽን አጀንዳ የነበሩ ክፍተቶችን ለመለየት ከአራት ጊዜ በላይ ግምገማዎች የተደረጉ ሲሆን፣ የጤና ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮች: የማኔጅሜንት አባለት እና የተጠሪ ተቋማት ኃላፊዎች በጤና ፍትሃዊነት ስትራቴጂ ዙሪያ ምክር አድርገዋል።

በሚኒስተሩ የጤና ስርዓት ማጠናከር ልዩ ድጋፍ ዳይሬክቶሬት ቡድን መሪ  አቶ ገሙ ቲሩ የጤና ፍትሃዊነትን ለማረጋገጥ አስቸጋሪ ያዳረጉት የቦታ አቀማመጥ፣ የትምህርት ደረጃ፣  የሃብት መጠን፣ በከተሞች እና በአርብቶ አደሮች እንዲሁም ልዩ ፍለጎት ባላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች የሚታየውን ልዩነት ለማጥበብ የአለም የጤና ድርጅት በሚያስቀምጠው መስፈርቶች መሰረት ለመስራት ስትራቴጂ መቀመጡን ተናግረዋል።

በአገር አቀፍ ደረጃ የጤና ፍትሃዊነትን ለማስጠበቅ የጤናው ሴክተር ሚና ብቻ ሳይሆን የሁሉም ሴክተር መስሪያ ቤቶች ድርሻ እንዲሆን ጥሪ የቀረበ ሲሆን፣ በቀጣይም ቅንጅታዊ አሰራሮችን ለማጠናከር ዕቅድ ተይዞ እንደሚሰራም ገልጸዋል።

በቀጣይም በተዘጋጀው ብሔራዊ የጤና ፍትሃዊነት ስትራቴጂ ዙሪያ የየክልሉ ከፍተኛ አመራሮች እና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የማህበራዊ ዘርፍና የአርብቶ አደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ከተወያዩበት በኋላ ጸድቆ ወደ ሙሉ ትግበራ ይገባል ተብሏል።

የጤና ሚኒስቴር በአንደኛው የጤናው ዘርፍ የትራንስፎርሜሽን አጀንዳ የጤና ፍትሃዊነትን ለማረጋገጥ በአራቱ ተመጣጣኝ ልማት የሚሹ ክልሎችና በተመረጡ አርብቶ አደር ዞኖች በጤናው ዘርፍ የተለያዩ ስራዎች ሲሰራ መቆየቱን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡