ግንቦት 25/2014 (ዋልታ) ታሪክ ለኢትዮጵያ ችግሮች የመፍትሄ አካል መሆን አለበት ሲሉ የታሪክ ተመራማሪው ኤሜሪተስ ባህሩ ዘውዴ (ፕ/ር) ገለጹ።
በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ አዘጋጅነት “የብዝሐ-ባህል አገር ተግዳሮቶች፤ አገራዊ መግባባትና የታሪክ ትምህርት ሚና በኢትዮጵያ አንዳንድ ምልከታዎች” በሚል መሪ ሀሳብ የሳይንሳዊ ገለጻና የውይይት መድረክ ተካሂዷል።
የመድረኩ አወያይ የታሪክ ተመራማሪው ኤሜሪተስ ባህሩ ዘውዴ(ፕ/ር) “ታሪክ የእውቀት መሰረት ቢሆንም የኮራንበት ታሪክ አሁን ላይ የምንበላላበት ሆኗል” ሲሉ ገልጸዋል።
ታሪክ የግጭት መንስኤ ሊሆን እንደማይችል በመጥቀስ፤ ታሪክ ለኢትዮጵያ ችግሮች የመፍትሄ አካል መሆን እንዳለበትም አስገንዝበዋል።
በውይይቱ ላይ የመነሻ ጽሁፍ ያቀረቡት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህር ግርማ ነጋሽ (ዶ/ር) በበኩላቸው ብዝሃነት እንደ መርገም ሊታይ አይገባም ያሉ ሲሆን ታሪክ ለሀገር ግንባታ ወሳኝ መነሻና መንደርደሪያ መሆኑን አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ሥራ አስፈጻሚ ዳይሬክተር ተከተል ዮሐንስ (ፕ/ር) አገራዊ መግባባት ላይ ያተኮሩ መሰል ውይይቶች በቀጣይነት እንደሚካሄዱ ገልጸዋል።
በመርኃ ግብሩ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽነር መስፍን አርአያ (ፕ/ር)፣ የታሪክ ምሁራን እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች መሳተፋቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የዛሬው ውይይት የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ሀገራዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ በየወሩ ትምህርታዊ መድረኮችን የሚያካሂድበት መርኃ ግብር አካል ነው::