አሸባሪው ትሕነግ በአፋር የቀጠለውን ጥቃት መንግሥትና የሚመለከታቸው ሁሉ ዝም ሊሉት እንደማይገባ ነዋሪዎች ጠየቁ

የካቲት 6/2014 (ዋልታ) አሸባሪው እና ወራሪው የትሕነግ ቡድን በአፋር ክልል ክልበቲ ረሱ ዞን እያደረሰ ያለውን ጥቃት አጠናክሮ መቀጡን ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡

ወራሪውን ቡድን እያደረሰ ያለውን ጥፋት መንግሥት እና የሚመለከተው አካል ዝም ሊለው እንደማይገባ ነው የጠየቁት፡፡

የሽብር ቡድኑ በአፋር ክልል ክልበቲ ረሱ አካባቢ ባደረሰው ወረራና ጥቃት የአበአላ፣ ኮናባ፣ እሪፕቲ ፣ መጋሌ እና በረሃሌ ወረዳ ነዋሪዎችን ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል፡፡

አሁን ላይም በሽብር ቡድኑ ጥቃት የተፈናቀሉ ዜጎች በኮሪ ወረዳ ጉዋህ ቀበሌ ተጠልለው እንደሚገኙ ኤፍቢሲ በስፍራው ተገኝቶ በመመልከት ዘግቧል፡፡

የሽብር ቡድኑ በማኅበረሰቡ ላይ እየፈጸመ ባለው የከባድ መሳሪያ ጥቃት ለከፍተኛ ሰቆቃ መዳረጋቸውን ነው ተፈናቃዮቹ የገለጹት።

ወራሪው ቡድኑ እያደረሰ ባለው ጥቃት ቤተሰብ ከቤተሰቡ ጋር ተለያይቶ መገናኘት እንዳይችል ማድረጉንም ነዋሪዎቹ ያስረዳሉ።

የሰብኣዊ ድጋፍ ከማድረግ አንፃር ትልቅ ትኩረትን እንደሚሻ እና በዘርፉ የተሰማሩ አካላት የበኩላቸውን እንዲወጡ ተፈናቃዮቹ ጥሪ አቅርበዋል፡፡