አንጋፋውና ሁለገቡ የኪነ ጥበብ ሠው – ተስፋዬ ሲማ

ተስፋዬ ሲማ

 

“ትያትር ህይወቴ ናት ” ይላል ሁለገቡ አርቲስት ተስፋዬ ሲማ። በብሄራዊ፣ በሀገር ፍቅር ፣ በአዲስ አበባ የቴአትርና ባህል አዳራሽ እንዲሁም በራስ ቴአትር ተዋናይ እና አዘጋጅ ሆኖ ሰርቷል::

በትምህርት ቤቶች ሚኒ ሚዲያዎችን በማቋቋም እንዲሁም በከተማዋ የቴአትርና የሙዚቃ ክበቦች እንዲመሠረቱና እንዲጠናከሩ በማድረግ ረገድ ስሙ ይነሳል፡፡ ዛሬ ላይ አንቱ የተባሉ የቴአትር፣ የሙዚቃ፣ የስነ ፅሁፍ እና የጋዜጠኝነት ባለሙያዎችን ያፈራ መሆኑም ይነገርለታል፤ ከያኒ ተስፋዬ ሲማ።

አንጋፋው የኪነ ጥበብ ሠው ተስፋዬ ሲማ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቴአትር ጥበባት በ1979 ዓ.ም ተመርቋል::

የትያትር ክፍል ኃላፊ በመሆን በአርሲ ክፍለ ሀገር መስራቱንና፣ ከዚያም የባህል መምሪያ ኃላፊ በመሆን ቦረና ራስ ገዝ አገልግሏል፡፡ በኋላም በአዲስ አበባ ባህልና ስፖርት ቢሮ የኪነ ጥበብ ዋና ክፍል ኃላፊ በመሆን ሠርቷል። ተስፋዬ ሲማ በሬዲዮ ድራማ በቴሌቪዥንና በፊልም ስራዎችም ሙያውን በብቃት የተወጣ የጥበብ ሰው ነው።

በተጨማሪም ለአምስት ተከታታይ ዓመታት በቴአትርና በስነ ፅሁፍ ዘርፍ ትምህርት ቤት በመክፈት የቴአትር አፃፃፍ፣ አዘገጃጀት፣ እንዲሁም በአተዋወን ብልሀት ከ400 በላይ ባለሙያዎችን አፍርቷል::

ተስፋዬ ቴአትር ለማሳየት ወደ ሀገረ አሜሪካ አቅንቶ ሳይመለስ ላለፉት 22 ዓመታት ከጣይቱ የኪነ ጥበብና የትምህርት ማዕከል ጋር በመሆን በርካታ ትያትሮችን በመፃፍ ፣ በማዘጋጀት እና በመተወን በመላው አሜሪካ ፣ ካናዳ፣ አውሮፓ እንዲሁም ደቡብ አፍሪካ የጥበብ ስራዎቹን አቅርቧል፡፡

ከያኒው ተስፋዬ ሲማ ከ22 ዓመታት ቆይታ በኋላ ወደ ሀገሩ ተመልሶ ባለፉት አንድ ዓመት ከስድስት ወራት ከፖሊስ ኦኬስትራ ጀምሮ ሀገሩን በኪነ-ጥበብ በማገልገል ላይ ይገኛል፡፡

በአሁኑ ወቅት የሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን ድርሰት የሆነውን “ሀሁ ወይም ፐፑ” ትያትር አዘጋጅቶ በኢትዮጵያ ብሄራዊ ትያትር ለተመልካች በማሳየት ላይ ይገኛል።

በፈቲያ ሁሴን