አዲስ ብድርና ቁጠባ ተቋም ወደ ባንክ አደገ

መስከረም 28/2014 (ዋልታ) አዲስ ብድርና ቁጠባ ተቋም በ3 ነጥብ 7 ቢሊየን የተከፈለ እና በ10 ቢሊየን ብር በተመዘገበ ካፒታል “ባንክ ኦፍ አዲስ” በሚል ወደ ባንክ ማደጉን አስታወቀ፡፡
የተቋሙ አመራሮችና ባለአክሲዮኖች በትላንትናው ዕለት ባካሄዱት ጉባኤ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ መመሪያ መሰረት በማድረግ ወደ ባንክ እንዲሸጋገር መወሰኑን የተቋሙ ማኔጅንግ ዳይሬክተር አቶ ዳምጠው አለማየሁ ገልጸዋል፡፡
ወደ ባንክ የተሸጋገረው ተቋሙ ከሌሎች ባንኮች በተለየ ሁኔታ ጣምራ አገልግሎትን ለህብረተሰቡ ለመስጠት እንደሚያስችል ከአዲስ አበባ ከተማ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
የአዲስ ብድርና ቁጠባ ተቋም በከተማ አስተዳደሩ ውስጥ ከመደበኛ ባንኮች የፋይናንስ አገልግሎት ማግኘት ለማይችሉ የህብረተሰብ ክፍሎች አዲስ አበባ ከተማ የስራ እድል ፈጠራ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ተብሎ በ1988 ዓ.ም በ5 አክሲዮኖች በ517 ሺሕ ብር የተከፈለ ካፒታል እና ከ1 ሚሊየን ብር በላይ በተመዘገበ ካፒታል መመስረቱን ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል፡፡