ኢትዮጵያ በ2020 የቶኪዮ ኦሎምፒክ 4 ሜዳሊያዎችን በማግኘት ውድድሯን አጠናቀቀች

ነሃሴ 3/2013 (ዋልታ) – ኢትዮጵያ በ2020 ቶኪዮ ኦሎምፒክ አራት ሜዳሊያዎችን በማግኘት ውድድሯን አጠናቃለች።

የቶኪዮ 2020 ኦሎምፒክ ጨዋታዎች ውድድር ዛሬ በሚደረጉ ውድድሮች ፍጻሜውን ያገኛል።

ኢትዮጵያም በአትሌቲክስ፣ በሴቶች ብስክሌት፣ በውሃ ዋና እና በወንዶች ወርልድ ቴኳንዶ የውድድር አይነቶች የተካፈለች ሲሆን፤ አራት ሜዳሊያዎችን በማግኘት ውድድሯን አጠናቃለች።

በውድድሩም 37 ኢትዮጵያውን አትሌቶች የተሳተፉ ሲሆን፤ ከእነዚህም መካከል በሴቶች ብስክሌት፣ በወንዶች ውሃ ዋና፣ እንዲሁም በወንዶች ወርልድ ቴኳንዶ በእያንዳንዳቸው አንድ አንድ አትሌቶች ተካፍለዋል።

ኢትዮጵያ በውድድሩ በአትሌት ሰለሞን ባረጋ አማካኝነት በ10 ሺህ ሜትር ወንዶች ሩጫ የወርቅ ሜዳሊያ እንዲሁም በአትሌት ለሜቻ ግርማ በ3 ሺህ ሜትር ወንዶች መሰናክል መድድር የብር ሜዳሊያ አግኝታለች።

በአትሌት ለተሰንበት ግደይ አማካኝነት በሴቶች በ10 ሺህ ሜትር እንዲሁም በአትሌት ጉዳፍ ፀጋዬ  በሴቶች 5 ሺህ ሜትር ሩጫ ውድድሮች የነሐስ ሜዳሊያዎችን አግኝታለች።

በ2020 ቶኪዮ ኦሊምፒክ ከተሳተፉ 200 በላይ ሀገራት መካከል 86ቱ የሜዳሊያ ሰንጠረዡ ውስጥ መግባት የቻሉ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ በአንድ ወርቅ፣ አንድ ብርና በሁለት ነሐስ ሜዳሊያ ከዓለም 56ኛ ከአፍሪካ ደግሞ 5ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።

አሜሪካ 39 የወርቅ፣ 40 የብርና 33 የነሐስ ሜዳሊያ ቀዳሚውን ደረጃ ይዛለች።

ቻይና በ38 ወርቅ፣ በ31 ብርና በ18 የነሐስ ሜዳሊያ ሁለተኛ ደረጃን ስትይዝ፤ አዘጋጇ ጃፓን 27 ወርቅ፣ 14 ብርና 17 ነሐስ ሜዳሊያ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።

አፍሪካዊቷ ኬኒያ አራት ወርቅ፣ አራት ብርና ሁለት የነሐስ ሜዳሊያ በመሰብሰብ በውድድሩ ከተካፈሉ የአፍሪካ ሀገራት ቀዳሚ  ስትሆን፤ ከዓለም 19ኛ ደረጃን ማግኘት ችላለች።

ዪጋንዳ በሁለት ወርቅ ፣አንድ ብርና አንድ ነሐስ ከዓለም 36ኛ፤ ከአፍሪካ ሁለተኛ እንዲሁም ደቡብ አፍሪካ በአንድ ወርቅና ሁለት ብር ከዓለም 52ኛ ከአፍሪካ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።

ግብጽ በአንድ ወርቅ፣ አንድ ብርና አራት ነሀስ ከዓለም 54ኛ ከአፍሪካ ደግሞ 4ኛ ደረጃን ይዛለች።

ኢትዮጵያ በቶኪዮ ኦሊምፒክ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ በርካታ አትሌቶችን ያሳተፈች ቢሆንም፤ እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር ከ1996 የአትላንታ ኦሊምፒክ በኋላ ዝቅተኛ የሚባል ውጤት ያስመዘገበችበት ሆኗል።