ኅዳር 27/2014 (ዋልታ) ኢትዮጵያ በ2015 የሚካሄደውን 17ኛውን የኢንተርኔት አስተዳደር ፎረም ታስታናግዳለች፡፡
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁርያ አሊ ከተባበሩት መንግስታት የኢኮኖሚና ማህበራዊ ጉዳዮች ምክትል ዋና ጸሐፊ ሉ ዤንሜን ጋር በፎረሙ ዝግጅት ዙሪያ በፖላንድ ተወያይተዋል።
በዓለም 3 ነጥብ 7 ቢሊዮን የሚሆነው ህዝብ ምንም አይነት የቴሌኮምና የኢንተርኔት አገልግሎት እንደማያገኝ የተናገሩት የተባበሩት መንግስታት የኢኮኖሚና ማህበራዊ ጉዳዮች ምክትል ዋና ጸሐፊ ሉ ዤንሜን ከዚህ ውስጥ ከፍተኛውን ቁጥር አፍሪካውያን ይይዛሉ ብለዋል።
በአፍሪካ የበይነ መረብ ግንኙነት ዝቅተኛ መሆኑን ያነሱት ዋና ጸሐፊው ኢትዮጵያ የምታስተናግደው ቀጣዩ ፎረም ይህንን ችግር ለመቅረፍ የመፍትሄ አቅጣጫዎች የሚጠቆሙበት ይሆናል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ገልፀዋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ በበኩላቸው አፍሪካ ከዲጂታል ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ለማድረግና ከመሰረተ ልማት ጋር የተያያዙ ችግሮቿን ለመፍታት የምታደርገው ጥረት በዚህ መልኩ ከተደገፈ መልካም ውጤት እንደሚመዘብ እምነታቸውን ገልፀዋል፡፡
በተለይ ከ60 በመቶ በላይ የሚሆነው ህዝብ ወጣት መሆኑ ቴክኖሎጂን ለማስፋፋትና ለልማት ለመጠቀም ትልቅ እድል ይፈጥራል ማለታቸውን የሚኒስቴሬ መረጃ ያሳያል።
ሀገራቸው ኢትዮጵያም የቴሌኮም ዘርፍ ማሻሻያ፣ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ፣የዲጂታል ክህሎትና ተጠቃሚነት ላይ በትኩረት እየሰራች መሆኑን ያብራሩት ሚኒስትር ዴኤታዋ፣ ሉ ዤንሚንና ቢሯቸው እያደረገ ላለው ትብብርና ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።