ኤጀንሲው የ45 አገልግሎቶችን የኦንላይን ስራ አስጀመረ

መስከረም 28/2014 (ዋልታ) የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ ከኤኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እና ከፔራጎ ሲስተም ጋር በመተባበር 45 አገልግሎቶችን ኦንላይን መስጠት የሚያስችል ስርዓት በመዘርጋት ስራ አስጀመረ።

በኦንላየን አገልግሎቶቹ ዙሪያ ከሲቪክ ማህበረሰቡ ጋር ግብዓት ለመሰብሰብና አሰራሩን ለማስተዋወቅ የሚያስችል ምክክር ተደርጓል፡፡

አገልግሎቶቹ ኦንላይን መሆናቸው የተጠቃሚዎችን እንግልት በመቀነስ የአገልግሎት እርካታን ለማሳደግ እንደሚረዳ የሲቪክ ማህበራት ድርጅቶች ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ ተናግረዋል፡፡

ዘመናዊ ቴክኖሎጂን የስራ መሳሪያ አድርጎ መገልገል ለስራ ቅልጥፍና ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለውም አንስተዋል።

በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ፕሮግራም ዳይሬክተር  ዶክተር ጀነራል አብዮት ባዩ ደህንነቱ የተጠበቀ፣ ቀልጣፋና ተጠያቂነት የሰፈነበት አሰራር በመዘርጋት የዜጎችን እንግልት ለመቀነስ እየሰራን ነው ብለዋል።

አገልግሎቶቹ ሳይቆራረጡ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉም አረጋግጠዋል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ አገልግሎቶቹን ለማዘመንና ቀጣይነት ባለው መልኩ ለመስራት መፈራረማቸውን ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡