ከተሞቻችን-ሆሣዕና

ሆሣዕና ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ክላስተር ከተሞች አንዷ ስትሆን የሀዲያ ዞን አስተዳደር ዋና መቀመጫም ናት፡፡ ከተማዋ ከአዲስ አበባ በደቡብ አቅጣጫ 230 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች።

ሆሳዕና ከባህር ጠለል በላይ 2 ሺሕ 217 ሜትር ከፍታ ላይ የምትገኝና ወይናደጋ የአየር ንብረት ያላት ሜዳማ እና ተዳፋታማ ተፍጥሯዊ የመሬት ገፅታን ተላብሳለች፡፡

በ1888 ዓ.ም እንደተቆረቆረች የምነገርላት ሆሳዕና የከተማዋ የቀድሞ መጠሪያ ዋቸሞ እንደነበርና ወደ ሆሳዕና የቀየሩት ራስ አባተ ቧያለው ሲሆኑ ተሹምው ወደ ስፍራው ባመሩበት ዕለት እየተከበረ የነበረውን የሆሳዕና በዓል ምክንያት በማድረግ እንደሆነም ይነገራል።

ሆሣዕና በስድስት ቀበሌዎች የተዋቀረች ከተማ ስትሆን ኬንተሪ፣ ገብረፃዲቅ፣ የአብስራ፣ ማሪያም፣ ሞቢል፣ ቁጭራ፣ አራዳ እና ካናል/መሳለሚያ በሚል የሚጠሩ የሰፈር ስያሜዎችም አሏት።

በከተማዋ የከፍተኛ የትምህርት ተቋም የሆነውን ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ጨምሮ፣ ሆሣዕና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ፣ ሆሳዕና መምህራን ኮሌጅ እንዲሁም ቅድስት ስላሴ፣ ዋቸሞ 1ኛ ደረጃ፣ አለሙ ወልደሀና 2ኛ ደረጃ እና ሌሎችም ትምህርት ቤቶች ይገኛሉ።

ሆሣዕና ምቹ የሆቴል እና ቱሪዝም እንቅስቃሴ የሚታይባት ከተማ ስትሆን ቪክትሪ፣ አዲላ፣ ዋኣኔ መላይ፣ ዎዜ ስታር፣ በረከት እና የመሳሰሉ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች እና ሌሎች ይጠቀሳሉ።

በከተማዋ በታላላቅ ጦርነቶች ላይ ተሰልፎ ለሀገሩ ትላልቅ ጀብዱዎችን የሰራ ታዋቂ የጦር አውሮፕላን አብራሪ እና የሀገር ባለውለታ የኮሎኔል በዛብህ ጴጥሮስ ሐውልትም ይገኛል፡፡

የሰላም አምባሳደር በሚል የምትሞካሸው ሆሣዕና የሀዲያ ብሔር ዘመን መለወጫ የሆነው “ያሆዴ” በድምቀት የሚከበርባት ከተማ ናት፡፡ በዕለቱ የበዓሉ ታዳሚዎችም “ሳሬዋና” ተብሎ በሚጠራው የሀዲያ ባህላዊ ልብስ ይደምቁበታል፡፡

“አተካና” በከተማው ከሚገኙ ተወዳጅ የሀዲያ ባህላዊ ምግቦች አንዱ ሲሆን በማህበረሰቡ ዘንድም እንደ ያሆዴ ላሉ ትላልቅ ክብረ በዓላት ወይም ልዩ ለሆኑ ዝግጅቶች የሚሰናዳ የምግብ አይነት ነው።

በዚህች ውብ ከተማ ተወልዳችሁ ያደጋችሁም ሆነ በተለያየ አጋጣሚ አይታችኋት ልዩ ትዝታን ያተረፋችሁ ትውስታችሁን አጋሩን።

መልካም ሳምንት!!

በአዲስዓለም ግደይ