በ14ኛው ክፍለ ዘመን አካባቢ በመንደርነት ተመስርታ በ1928 ዓ.ም ወደ አውራጃነት ያደገችው ሽረ በአሁን ሰዓት የሰሜን ምዕራብ ትግራይ ክልል ፈርጥ ከተማ ስትሆን የታህታይ ቆራሮ ወረዳ አስተዳደር ማዕከል ነች።
ሽረ ከባህር ጠለል በላይ 1ሺሕ 953 ሜትር አማካኝ ከፍታ እና ወይና ደጋ የአየር ፀባይ ያላት በኮረብታማ መልከዓ ምድር የተከበበች ከተማ ስትሆን ከመዲናችን አዲስ አበባ በስተሰሜን 1ሺሕ 87 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ትገኛለች።
ከስያሜዋ ጋር በተያያዘ በጊዜው የነበረ ጀግና ኩናማዎችን አሸንፎ ከተማውን እንደተቆጣጠረ ለሕዝቡ ማሸነፉን ለመግለፅ በትግርኛ ቋንቋ “ስዒረ” ማለቱን ተከትሎ ሽረ ተብላ መጠራት እንደጀመረች በአፈታሪክ የሚነገር ሲሆን ጥንታዊቷ የቅድስት ስላሴ ገዳም ከከተማዋ ስም ጋር ተቀፅላ ሆና ትጠራለች።
በጣሊያናዊ መሀንዲስ ማስተር ፕላን የተሰራላት ሽረ ታዋቂ ከሆኑ የሰፈር ስያሜዎቿ መካከል ኣጓዱ፣ ተክልዬ(24)፣ ዲቦራ፣ እንዳ ጀርመን፣ ቀይ ለከፍ፣ ድልድል፣ መድየ እና ቄራ ተጠቃሾች ናቸው።
በከተማዋ አማካኝ ስፍራ ላይ ከሀገር ባለውለታ የጦር ጀነራሎች መካከል ስሙ በጉልህ የሚነሳው የሜጀር ጀነራል ሓይሎም አርአያ ሐውልት ይገኛል።
ሽረ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች የሚገኙባት ከተማ ስትሆን ከእነዚህም መካከል ገባር ሽረ፣ ቃሌም፣ አፍሪካ፣ ሀዳስ ኢንተርናሽናል እና ደጀና ሆቴሎች ተጠቃሽ ናቸው።
በከተማዋ ፀሀይ፣ ሕብረት እና እምባ ዳንሶን ጨምሮ 12 አንደኛ እና 3 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚኙ ሲሆን በተጨማሪም የአክሱም ዩኒቨርሲቲ ሽረ ካምፖስ፣ ኦክስፎ ቴክኖሎጂ፣ የግብርና እና የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ይገኛሉ።
“ማይ አድራሻ” ከሽረ ከተማ በ2 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የሚገኝ ጥንታዊ አርኪኦሎጂካል ስፍራ ሲሆን ከክርስቶስ ልደት በፊት 1250 ዓመት ዓለም ላይ የነበረ ከተማ እንደሆነ የሚነገርለት ቅርስ ነው።
ለመኖር ምቹ የሆነችው ሽረ ውብ፣ ሰላማዊ እና እንግዳ ተቀባይ ሕዝብ ተቻችሎ በፍቅር የሚኖርባት ከተማ ናት። በተጨናነቁ የገበያ ስፍራዎቿ፣ በጥር ወር በድምቀት በሚከበረው ዓመታዊ የስላሴ ንግስ በዓል እና ተወዳጅ በሆነው የጠላ መጠጥ ትታወቃለች።
ሽረ እንዳሥላሰ የተለያዩ የሀገር ባለውለታዎችን እና የጥበብ ሰዎችን ያፈራች ሲሆን የአሁኑ መቻል እግርኳስ ክለብ ምክትል አሰልጣኝ ዳንኤል ፀሀዬም የከተማዋ ፍሬ ናቸው።
በከተማዋ ተወልዳችሁ ያደጋችሁም ሆነ በተለያየ አጋጣሚ አይታችኋት ልዩ ትዝታን ያተረፋችሁ ትውስታችሁን አጋሩን።
መልካም ሳምንት!
በአዲስዓለም ግደይ