ከተሞቻችን – አሰላ

አሰላ በኦሮሚያ ክልል በደቡብ ምስራቅ የሀገራችን ክፍል የምትገኝ ስትሆን የአርሲ ዞን ዋና መቀመጫ ናት፡፡ በ1930 ዓ.ም አካባቢ እንደተመሰረተች የሚነገርላት አሰላ ከአዲስ አበባ 175 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች፡፡

ከተማዋ ከባህር ጠለል በላይ 2 ሺህ 430 ሜትር ከፍታ ላይ የምትገኝ እና ደጋማ የአየር ፀባይን የተላበሰች ናት።

“አሰላ” የሚለው ቃል ከአርሲ ኦሮሞ ወገን ከሆነው የጎሳ መጠሪያ እንዳገኘች ይነገራል፡፡

አሰላ በነዋሪዎቿ አብሮነት እና ተቻችሎ መኖር የምትታወቅ ድንቅ ከተማም ናት።

የአሰላ ከተማ የተለያዩ ታዋቂ የሰፈር ስያሜዎች ያሏት ሲሆን ደራርቱ ሰፈር፣ ሚካኤል ሰፈር፣ ሆላ ሲቀቤ፣ አርዱ፣ ባንክ ቤት ለአብነት ተጠቃሽ ናቸው።

በከተማዋ የተለያዩ የትምህርት ተቋማት የሚገኙ ሲሆን አርሲ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ አሰላ አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ፣ ሐምሌ 19፣ አሰላ አንድነት፣ ማርቭል፣ ሮቦት ሜዲካል ኮሌጅ እና ጭላሎ ትምህርት ቤቶች ይጠቀሳሉ።

የከተማዋ ድምቀት ከሆኑ ታዋቂ ሆቴሎች መካከልም ላቀው፣ ከታር፣ ጭላሎ፣ ቴዎድሮስ፣ ራስ ዳርጌ፣ ኤል ቪ እና ሌሎችም ይገኙባታል።

ከከተማዋ በቅርብ ርቀት የሚገኘው እና 4ሺሕ 036 ሜትር ከባህር ጠለል በላይ ከፍታ ያለው የጭላሎ ተራራ የከተማዋ የጎብኝ መስህብ ሥፍራ ነው፡፡

በተራራው አናት ላይ የተለያዩ አጥቢ እንስሳት እና አዕዋፋት ይገኙበታል፡፡ በቀዝቃዛ አየር ጸባዩና እና ለአይን ዕይታ በሚማርከው ገጽታው ምርጥ የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራም ነው የጭላሎ ተራራ።

በከተማዋ የአሰላ ሙዚየም የሚገኝ ሲሆን በውስጡም የአርሲ ኦሮሞ ባህላዊ አለባበስን ጨምሮ የሙዚቃ መሳሪያዎች፣ የእጅ ስራ ውጤቶች እና የሀውልት ስዕሎች ይገኛሉ።

የአሰላ ምድር በዓለም መድረክ ታዋቂና እንቁ አትሌቶችን አፍርታለች።

በኪነ ጥበቡም ዘርፍም ስመጥር የሀገር ባለውለታዎችን ማፍራት የቻለች ከተማ ናት አሰላ፡፡

በዚህች ውብ ከተማ ተወልዳችሁ ያደጋችሁ እንዲሁም በተለያየ አጋጣሚ አይታችኋት ልዩ ትዝታን ያተረፋችሁ ትዝታችሁን አጋሩን። መልካም ሳምንት!!

በአዲስዓለም ግደይ