ከአሳማ የተወሰደ ኩላሊት ንቅለ ተከላ የተደረገለት ግለሰብ ሕይወቱ አለፈ

ከአሳማ የተወሰደ ኩላሊት ንቅለ ተከላ የተደረገለት ሪቻርድ ስሌይማን


ለመጀመሪያ ጊዜ ከአሳማ የተወሰደ ኩላሊት ንቅለ ተከላ የተደረገለት ግለሰብ ሪቻርድ ስሌይማን የሚባል አሜሪካዊ ነው። ንቅለ ተከላው ከተከናወነለት ከሁለት ወር በኋላ ሕይወቱ ሊያልፍ መቻሉን የማሳቹሴትስ አጠቃላይ ሆስፒታል ገልጿል፡፡

ሆስፒታሉ አክሎም የስሌማን ሞት በንቅለ ተከላው ምክንያት መሆኑን የሚያመለክት ነገር እንደሌለ ነው ያስታወቀው፡፡

በማሳቹሴትስ ሆስፒታል አራት ሰዓት በፈጀ ቀዶ ጥገና ነበር ለመጀመሪያ ጊዜ በዘረ-መል ምህንድስና የተሻሻለ የአሳማ ኩላሊት በሰው አካል ውስጥ መትከል የተቻለው፡፡

ስሌማን ከ6 ዓመት በፊት በዚሁ ሆስፒታል ውስጥ ሕይወቱ ካለፈ ለጋሽ ተወስዶ የኩላሊት ንቅለ ተከላ ተደርጎለት የነበረ ሲሆን የተፈለገውን ያክል ውጤታማ ሊሆን አልቻለም። በዚህም መሰረት የስኳርና የደም ግፊት የነበረበት ስሌማን በድጋሚ ከ6 ዓመት በኋላ የአሳማ ኩላሊት ንቅለ ተከላ ለማድረግ ተገዶ ነበር።

ህክምናውን ያደረጉለት ዶክተሮች ኩላሊቱ ለዓመታት ሊሰራ እንደሚችል መላምተቸውን አስቀምጠው የነበረ ቢሆንም ስሌማን ሕይወቱ ሊያልፍ መቻሉን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡

ይሁን እንጂ ስሌማን ‘የዜኖ-ትራንስፕላንቴሽን’ መስክን ወደፊት እንዲራመድ ላሳደረው እምነት እና ፈቃደኝነት በጣም እናመሰግናለን” ሲል ሆስፒታሉ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል።