ከእንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፉ በሽታዎች


ጤና ደጉ

ከእንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፉ በሽታዎች (ዙኖቲክ ዲዚዝስ) በዓለም ላይ ከአንድ ቢሊዮን በላይ ሰዎችን ለህመም የሚዳርግ ነው፡፡ በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ደግሞ የህልፈተ ህይወት ምክንያት እንደሚሆን ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡

በቅርቡ ብቻ የተከሰተውን የዙኖቲክ በሽታ ጥሩ ምሳሌ የሆነውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽን ብንወስድ ዓለምን ግልብጥብጧን ያወጣ ጉዳት አድርሷል፡፡ በፈረንጆቹ 2019 የተከሰተው ኮቪድ-19 ዓለም አቀፍ ወረርሽን የስነልቦናዊና ማህበራዊ ጉዳቱን ሳንቆጥር ከ7 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ሞት እና ከ 9 ትሪሊዮን በላይ የኢኮኖሚ ኪሳራ ማስከተሉን መረጃዎች መለክታሉ፡፡

ከእነዚህ በሽታዎች መካከል ኢቦላ፣ የዕብድ ውሻ በሽታ፣ አባ ሰንጋ፣ ኮቪድ፣ የዝንጀሮ ፈንጣጣ፣ አንትራክስ፣ የወፍ ጉንፋን፣ የስምጥ ሸለቆ ትኩሳት እና የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ፡፡

በአፍሪካ ከእንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፉ በሽታዎች አሃዝን በተመለከተ በፈረንጆቹ ከ2012 እስከ 2022 የወጣው መረጃ ከዛ በፊት ከነበረው የ63 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን የዓለም ጤና ድርጅት አስታውቋል፡፡

መረጃው ጨምሮም በዓለም ዙሪያ የሰው ልጅን ከሚያጠቁ ነባር ተላላፊ በሽታዎች 60 በመቶ እንዲሁም አዲስ ከሚከሰቱ በሽታዎች 75 በመቶው ከእንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፉ በሽታዎች ናቸው ብሏል፡፡

ለሽታው መስፋፋት አስቻይ ሁኔታዎች

በሽታዎቹ በከፍተኛ ፍጥነት እንዲዛመቱና እንዲጨምሩ በምክንያትነት የቀረቡት ደግሞ የከተሞች መስፋፋት፣ ከፍተኛ የሰዎች ፍልሰት፣ የመጓጓዣ አውታሮች መስፋፋት ይጠቀሳሉ፡፡ ኮሮና በአጭር ጊዜ ዓለምን ያጥለቀለቀበት ጥሩ ማሳያ ሊሆን ይጭላል፡፡ በተጨማሪም እንስሳት በብዛት ለምግብነት መዋላቸው፣ የዱር እንስሳት ስነ ምህዳር መዛባት፣ የደኖች መጨፍጨፍ ወዘተ እንደሆኑ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

ከእንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፉ በሽታዎች በኢትዮጵያ

በኢትዮጵያ በብዛት የሚከሰቱት ከእንስሳት ወደ ሰው ከሚተላለፉት በሽታዎች መካከል የእብድ ውሻ በሽታ፣ አባ ሰንጋ(አንትራክስ)፣ ውርጃን ሚስከትል በሽታ፣ የወፍ ጉንፋንና የስምጥ ሸለቆ ትኩሳት መሆናቸውን የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል፡፡

ለዚህም እንደምክንያት የሚጠቀሰው 85 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ ኑሮው ከእንስሳት ሀብት ጋር የተያያዘ በመሆኑ እንደሆነ ይነገራል፡፡ እንስሳት የገቢ ምንጭ እንዲሁም ስጋቸውንና ወተታቸውን በምግብነት በሰፊው ጥቅም ላይ ይውላል፡፡ ይህም በሽታው በቀላሉ ጥሬ ወተትና ስጋ በመመገብ በሽታው ካለባቸው እንስሳት ወደ ሰው በቀላሉ እንዲተላለፍ ስለሚያስችል ነው፡፡

ጥሬ ስጋ መመገብ በከተማም ይሁን በገጠሩ የአገራችን ክፍል የተለመደ ነው፡፡ ያልበሰለ ስጋና ወተት መመገብ ደግሞ ለበሽታው መተላለፊያ ግንባር ቀደም መንገድ ነው፡፡ ነገሩን የባሰ አስቸጋሪ የሚያደርገው ደግሞ ለምግብነት የሚታረዱት አብዛኞቹ እንስሳት በቄራ ተመርምረው ያልታረዱ ስለሚሆኑ ነው፡፡ ለዚህ ጥሩ ማሳያው ለበዓል በየቤቱ የሚታረዱት እንስሳት ይህን ሂደት ሲያልፉ አይታዩም፡፡

ችግሩን ለመፍታት የጤና ሚኒስቴር ከዓለም የጤና ድርጅት ጋር በመሆን አንድ የጤና መርህ ተግባራዊ እያደረገ ነው፡፡ መርሁ በዋናነት በሰው ልጅ እንስሳትና አካባቢ የሚፈጠሩ የጤና ችግሮች ተመጋጋቢነት እንዳላቸው ያስገነዝባል፡፡ ግቡም በትብብር እነዚህ ሶስት አካላት ጤንነታቸው የሚረጋገጠበትን አሰራር መተግበር ነው፡፡

በዚህም የእንስሳት ህክምና አገልግሎት መስጫና የሰው ኃይል ማስፋፋት፣ የባለድርሻ አካላትን የተቀናጀ አሠራር ማጠናከር እንዲሁም በከተሞች አካባቢ ዘመናዊ የቄራና ጤናማ ስጋ አቅርቦት ላይ መስራት አስፈላጊ መሆኑ ይታመናል፡፡

በቴዎድሮስ ሳህለ

ምንጭ
• ግብርና ሚኒስቴር
• ጤና ሚኒስቴር
• ሲዲሲ አፍሪካ
• የዓለም ጤና ድርጅት
• ሲዲሲ
• ቪኦኤ አማርኛ
• ቢዮሜድ ሴንትራል