ከ18 እስከ 24 ወራት ይሰጥ የነበረው የቲቢ በሽታ ህክምና ከ9 እስከ 12 ወራት በሚሰጥ መድሐኒት ተተካ

መድሃኒትን ለተላመደ ለቲቢ በሽታ ከዚህ በፊት ከ18 እስከ 24 ወራት ይሰጥ የነበረው የህክምና አገልግሎት ከ9 እስከ 12 ወራት በሚሰጥ መድሐኒት መተካቱን ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ህክምናው ከዚህ ቀደም በመርፌና በሚዋጥ መድሃኒት መልክ ሲሰጥ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፣ አሁን በሚዋጥ መድሃኒት መተካቱም ነው የተገለጸው፡፡

በዛሬው ዕለት መድሐኒቱን የተላመደ የቲቢ በሽታ ህክምና ለሚከታተሉ ታካሚዎች በአጭር ጊዜ አገልግሎት ማግኘት የሚያስችል የማስጀመሪያ ስነ- ስርዓት ተካሄዷል፡፡

በዚሁ ወቅት የበሽታ መከላከልና መቆጣጠር ምክትል ዳይሬክተርና የብሔራዊ ቲቢ መከላከል ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ታዬ ለታ መድሃኒቱን የተላመደ የቲቢ በሽታ በማህበረሰቡ ዘንድ እየፈጠረ ያለው ተጽዕኖ ከባድ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የጤና ሚኒስቴር የበሽታውን አሳሳቢነት በመመልከትና ትኩረት በመስጠት ስርጭቱ እንዳይስፋፋ በመከላከልና በበሽታው ለተያዙ ህሙማን ተገቢውን የህክምና አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት በበሽታው ዙሪያ ጥናት እንዲደረግ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ኢትዮጵያም የጥናቱ ተሳታፊ በመሆን ውጤታማ የሆነ ጥናት ማካሄዷን አንስተዋል፡፡

አዲሱ የሚዋጠው መድሐኒት ለህሙማኑ ከፍተኛ ጫና የሚቀንስና እፎይታን እንደሚሰጥ በመግለጽ፣ ህክምናውን ለማስጀመር አስፈላጊው ዝግጅት እንደተጠናቀቀም አስታውቀዋል፡፡

የጤና ባለሙያዎችና የሚመለከታቸው አካላት የህክምና አገልግሎቱ የተሳካ እንዲሆን የበኩላቸውን እንዲወጡ አቶ ታዬ ማሳሰባቸውን ከጤና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡