ወልቂጤ – ከተሞቻችን

ከተመሠረተች ከ150 ዓመታት በላይ ያስቆጠረችው ወልቂጤ በማዕከላዊ ኢትዮጰያ ክልል የምትገኝ ከተማ ናት።

ወልቂጤ ከተማ ከመዲናችን አዲስ አበባ በስተደቡብ ምእራብ 155 ኪ.ሜ ርቀት ላይ እንዲሁም ከባህር ጠለል በላይ በ1ሺሕ 910 ሜትር ከፍታ ላይ ትገኛለች፡፡ የአየር ንብረቷ ወይና ደጋ ሲሆን ሜዳማ የመሬት አቀማመጥ አላት።

የከተማዋ ጠቅላላ የቆዳ ስፋት 7ሺሕ 260 ሄክታር ሲሆን በዞኑ ካሉት ወረዳዎች ውስጥ የቸሃ፣ የአበሽጌና የቀቤና ወረዳ ያዋስኗታል፡፡

በከተማዋ የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ የፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ፣ የመሰናዶ ትምህርት ቤቶች፣ ከአራት በላይ አገልግሎት በመስጠት ላይ ያሉ የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች  እና ሌሎችም የትምህርት ተቋማት ይገኛሉ።

የንግድ እንቅስቃሴ በሰፊው የሚካሄድባት የወልቂጤ ከተማ ደረጃቸውን የጠበቁ እና ዘመናዊ ሆቴሎችም አሏት። ከእነዚህም መካከል ስራኖ፣ የጆካ፣ ኢንቲሳር፣ ባሮክ፣ ረድኤት እና ሌሎችም በጥቂቱ ተጠቃሽ ናቸው።

በዞኑ ከሚገኙ የቱሪዝም መስህቦች መካከል የጢያ ትክል ድንጋዮች መካነ-ቅርስ አንዱ ሲሆን፣ በ12ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አካባቢ እንደተተከለ ይነገራል። ሀገራችን በዩኔስኮ ካስመዘገበቻቸው ቅርሶች አንዱ ነው።

ዓመቱን ሙሉ ያለማቋረጥ የሚፈሱት የዋቤ እና የመጌቻ ወንዝ በከተማዋ ዙሪያ የሚገኙ ሲሆን በተጨማሪም የዘቢደር ተራራም አንዱ የአካባቢው መገለጫ የሆነ እና ከባህር ጠለል በላይ 3 ሺሕ 700 ሜትር ከፍታ ያለው ድንቅ ተፈጥሮ ነው።

ተቻችሎ የመኖር ተምሳሌት የሆነችው ወልቂጤ ስራ ወዳድነት እና እንግዳ ተቀባይነት ባህላቸው ያደረጉ ህዝቦች መገኛ፤ ታዋቂ የሀገር ሀብት የሆኑ ግለሰቦችንም ያፈራች ምድር ናት።

በዚህች ውብ ከተማ ተወልዳችሁ ያደጋችሁ እንዲሁም በተለያየ አጋጣሚ አይታችኋት ልዩ ትዝታን ያተረፋችሁ ትዝታችሁን አጋሩን።

መልካም ሳምንት!

በአዲስዓለም ግደይ