ዊኪሊክስ ያወጣቸው 10 ታላላቅ  ሚስጢሮች

የዊኪሊክስ መስራች ጁሊያን አሳንጅ ከ14 ዓመታት እስርና የፍርድ ቤት ክርክር በኋላ ሰኞ ዕለት ነጻ ተለቋል።

አሳንጅ እ.ኤ.አ በ2006 ዊኪሊክስ የተባለ የመንግስትና ኩባንያዎችን ወንጀል ማጋለጫ በይነ መረብ ይፋ አደረገ። በይነ መረቡ በዋናነት መረጃ አፈትላኪ ግለሰቦች ስማቸውን ሳይገልጹ ሚስጢራዊ መረጃዎችን እንዲልኩ ያስችላል።

አውስትራሊያዊው የ52 ዓመቱ አሳንጅ የአሜሪካን ወታደራዊና ሌሎች ከ10 ሚሊዮን በላይ ሚስጢሮቿን በበይነ መረቡ አደባባይ አውጥቶባታል።

በዚህም ሰውዬውን በህግ ለመቅጣት በርካታ ሙከራ አድርጋለች። ከእንግሊዝ ተላልፎ እንዲሰጣትም ያልፈነቀለችው ድንጋይ አልነበረም። በፈረንጆቹ 2012 በለንደን የኢኳዶር ኤምባሲ የፖለቲካ ጥገኝነት ተሰጥቶት ለሰባት ዓመታት ቆይቷል።

በኢምባሲ ቆይታው ከፍተኛ የባህርይ ችግር በማሳዬቱ በኢኳዶር መንግስት ፈቃድ የለንደን ፖሊስ በቁጥጥር ስር አውሎት የዋስትና ህግ ጥሰሃል ተብሎ ለ50 ሳምንት በቤልማርሽ እስር ቤት ታሰረ።

የጁሊያን አሳንጅ ዊኪሊክስ ያጋለጣቸው አስር ታላላቅ ሚስጥሮች

  1. የአፍጋኒስታን የጦርነት ሚስጢር

አሜሪካ በፈረንጆቹ ከ2001 ጀምሮ በአፍጋኒስታን እያካሄደችው በነበረው ጦርነት ዙሪያ ለህዝብ ከተገለጸው መረጃ የተለዬና የጦርነቱን ትክክለኛ ገፅታ የሚገልፅ 90 ሺህ መረጃዎችን በበይነ መረቡ ይፋ አደረገ። አሜሪካ ከታሊባን ጋር በምታደርገው ጦርነት የረባ ድል ማስመዝገብ አለመቻሏን ያመለክቱ ነበር መረጃዎቹ።

  1. የኢራቅ ጦርነት

ዊኪሊክስ አሜሪካ በፈረንጆቹ ከ2003 ጀምሮ በኢራቅ የምታካሂደውን ጦርነት በተመለከተ 400 ሺህ ሚስጢራዊ ዶሴዎችን አወጣ። ከ2004 እስከ 2009 በተካሄደው ጦርነት በኢራቅና በአፍጋኒስታን በተካሄደው ጦርነት የሞቱ ሲቪሎች ቁጥር አሜሪካ ለህዝብ ከገለጸችው ከፍ ያለ ሆኖ ተገኘ።

         3. በአይቮሪ ኮስት የተደፋው መርዛማ ኬሚካል

በአይቮሪ ኮስት ለ108 ሺህ ሰዎች የጤና መታወክ ምክንያት የሆነ መርዛማ ኬሚካል ስለመደፋቱ አጋልጧል። በፈረንጆቹ 2006 ዋና መስሪያ ቤቱ ሲንጋፖር የሆነ ትራፊጉራ የተባለ ኩባንያ 560 ሺህ ሊትር መርዛማ ኬሚካል አቢጃን ወደብ አካባቢ አስወገደ። መርዛማ ኬሚካሉ ቆዳን፣ አይንንና ሳምባን የሚያቃጥልና ሰዎች እንዲያስታውኩ እንዲሁም ወደታች እያለ ራሳቸውን እስከመሳት የሚያደርስ ጉዳት አድርሷል። ለሶስት ሰዎችም ሞት ምክንያት ሆነ።

      4. የአሜሪካ ሚስጢራዊ  የዲፕሎማቲክ ሰነዶች 

የአሜሪካ ዲፕሎማሲ ፐብሊክ ቤተ መፅሀፍ የተባለ የመረጃ ቋት በማዘጋጀት አገሪቱ ከ1966 እስከ 2010 በ274 ኤምባሲዎቿና ቆንስላዎቿ በኩል የሰበሰበቻቸውን ከ 3 ነጥብ 33 ሚሊዮን በላይ ሚስጠራዊ ዶሴዎች ለአደባባይ አሰጣ። ከወጣው ሚስጢር ውስጥ ከፍተኛ የወዳጅ አገር መሪዎች፣ የራሷ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ከፍተኛ ኃላፊዎች ገበናዎች ይገኙባቸዋል።

  1. የጋዜጠኞችና የሲቪሎች ግድያ በባግዳድ

በ2010 ከተለቀቁት አደገኛና አሳፋሪ የአሜሪካ ሚስጥራዊ መረጃዎች አንዱ የሮይተርስ ጋዜጠኞቹ ናሚር ኑር ኤልዲን እና ሳኢድ ችማግን ጨምሮ በርካታ ሲቪሎች ከአሜሪካ የጦር ሄሊኮፍተር በተተኮሰ ሚሳኤል በባግዳድ ከተማ የተገደሉበት የቪዲዮ መረጃ ነው። በ2007 በባግዳድ ከተማ ሰዎቹ ሲገደሉ ከሄሊኮፍተሩ ውስጥ ሆኖ የተቀረጸ የቪዲዮ መረጃ ነበር ዊኪሊክስ እጅ የገባው። ይህ መረጃም በአሜሪካ ላይ ከፍተኛ ዓለም አቀፍ ውግዘትን አስከተለባት።

  1. የጓንታናሞ ዶሴ

ዊኪሊክስ በአሜሪካ መንግስት ተይዘው በጓንታናሞ እስር ቤት በነበሩ ከ800 በላይ በሽብር ወንጀል የተጠረ|ጠጠሩ እስረኞች ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎችን የሚዳስስ በሺዎች የሚቆጠር ገፅ ያላቸው መረጃዎች ደርሰውታል። ከ2002 እስከ 2008 የተሰበሰቡ እንደሆነ የተገለጹት እነዚህ መረጃዎች አሜሪካ በተደጋጋሚ የጀኔቫ ስምምነትን መጣሷን የሚያሳዩ ናቸው። በጓንታናሞ ከነበሩት የፓኪስታንና የአፍጋን ዜግነት ያላቸው እስረኞች 150 ያህሉ ነፃ መሆናቸው በኋላ ተረጋግጧል።

  1. የሶሪያ ዶሴ

ዊኪሊክስ ሶሪያን የተመለከቱ ከሁለት ሚሊዮን በላይ መረጃዎችንም አውጥቷል። መረጃዎቹ ከ2006 እስከ 2012 ባለው ጊዜ ከፍተኛ የሶሪያ ባለስልጣናት ከፕሬዝዳንት በሽር አላሳድ ጋር የተደረጉ የኢሜይል ልውውጦች ናቸው።

በመረጃው አውሮፓ ኩባንያዎች ጭምር በመንግስት ላይ ተቃውሞ ያሰሙ ሲቪሎችን በማፈን ተሳታፊ እንደነበሩ ይፋ አውጥቷል።

  1. የብሔራዊ የጸጥታ ኤጀንሲ (NSA) ስለላ

ዊኪሊክስ ከ2015 እስከ 2017 ባለው ጊዜ ካወጣቸው መረጃዎች ውስጥ የአሜሪካው አገር ውስጥ ጸጥታ ኤጀንሲ (NSA) በህገ ወጥ መንገድ የዜጎችን መረጃ ጠልፎ እንደሚበረብር የሚያጋልጡ ነበሩ። ተቋሙ የወቅቱ የተባበሩት መንግስታት ዋና ጸሀፊ ባንኪ ሙንን እና የጀርመኗን ቻንስለር አንጌላ መርክልን ስልክ ሁሉ ጠልፎ ሲያደምጥ እንደነበር ይፋ ሆነ። በዚህም ወዳጅ አገሮች ጭምር በድርጊቱ ከፍተኛ ተቃውሞ መፍጠሩና የነበራቸውን ወዳጅንት መሸርሸሩ ይታወሳል።

  1. የሶኒ ፒክቸርስ ኮምፒውተር ስርሰራ

በፈረንጆቹ 2015 ዊኪሊክስ ከግዙፉ የፊልም ሰሪ ኩባንያ ከሆነው ሶኒ ፒክቸርስ መረጃ ቋት የተመነተፉ 170 ሺህ ያህል ኢሜይሎችና 20 ሺህ ዶክመንቶችን በዌብ ሳይቱ ለቀቀ። የኮምፒውተር ስርሰራው የተከናወነው ሶኒ ፒክቸርስ ሰሜን ኮሪያውን መሪ ኪም ጆን ኡንን በመግደል ዙሪያ የሚያጠነጥን የፈጠራ ፊልም ሰርቶ ሊለቅ በነበረበት ወቅት ነው። ከተገኙት መረጃዎች ውስጥ ሶኒ ለወንድ ተዋናዮች ከሴት እኩዮቻቸው አንጻር በጣም ከፍ ያለ ደመወዝ ሲከፍል እንደነበር በማጋለጡ ከፍተኛ ውግዘትና ተቃውሞ እንዲገጥመው ምክንያት ሆኖ ነበር።

  1. የዲሞክራቲክ ፓርቲ የኢሜይሎች

ዊኪሊክስ በ2016 በአሜሪካ የዲሞክራቲክ ፓርቲ ብሔራዊ አመራሮች የተለዋወጧቸውን ከ19 ሺህ በላይ የሚሆኑ ኢሜይሎችና 8 ሺህ አባሪዎች በዌብሳይቱ ይዞ ብቅ አለ። በመረጃውም በ2016 ፕሬዝዳንታዊ ምርጫው ውድድር ወቅት በፓርቲው አመራሮች መካከል መከፋፈል መኖሩን አመልክቷል። ሚስጥሩ አደባባይ መዋሉን ተከትሎ በርካታ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ስልጣን ለመልቀቅ ምክንያት ሆነ። ሂላሪ ክሊንትንም በዶናልድ ትራምፕ እንድትሸነፍ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ አስተዋፅኦ ነበረው።

ጁሊያን አሳንጅ ከእስር የተለቀቀው በተከሰሰበት ወንጀል ጥፋተኝነቱን አምኖ ሲሆን በእጁ ያሉትን ሚስጥራዊ ሰነዶች ለማጥፋት ግዴታ ውስጥ መግባቱን አልጃዜራ ዘግቧል።