ነሃሴ 12/2013 (ዋልታ) – የሀገር ሉዓላዊነትን አደጋ ላይ ለመጣል በሚንቀሳቀስ የትኛውም ኃይል ላይ የሚወሰደው ምሕረት የለሽ እርምጃ የሚቀጥል መሆኑን የኦሮሚያ ክልል መንግሥት አስታወቀ።
የክልሉ መንግሥት ዛሬ ባወጣው መግለጫ፣ የክልሉ ሕዝብ አሸባሪውን ሸኔ በማውገዝ በተለያዩ የክልሉ ዞኖች እና ከተሞች በራስ ተነሳሽነት ላካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ ምስጋና አቅርቧል።
ሕዝቡ የሸኔን የጥፋት ድርጊት እና የክፋት ሐሳብ በመረዳት በቂ ዝግጅት አድርጎ ይህን የሽብር ቡድን ማውገዙ ከፍተኛ የፖለቲካ ብስለት ላይ መድረሳችንን የሚያመላክት ነው ብሏል።
ሕዝቡ አካባቢውን ከጠላት ለመጠበቅ በቂ ዝግጅት ማድረጉንም አስመስክሯል ነው ያለው።
ሰላማዊ ሰልፉ በሰላም እንዲጠናቀቅ አስተዋፅኦ ላደረጉ የኅብረተሰብ ክፍሎች እና የመንግሥት መዋቅሮችም ምስጋና አቅርቧል።
ተመሳሳይ ሰላማዊ ሰልፎችን ለማድረግ የተዘጋጁ የክልሉ ከተሞች እና ዞኖች እንዳሉ የገለጸው የክልሉ መንግሥት፣ እነዚህ ከተሞች እና ዞኖች ነዋሪዎች በአንድ በኩል የአሸባሪውን የሸኔ ቡድን በማጋላጥ በሌላ በኩል ደግሞ የአካባቢውን ሰላም በፅናት በመጠበቅ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቋል።
የኦሮሞን ሕዝብ ነፃነት ለማስጠበቅ ትክክለኛ የትግል መንገድ ነው ብለው በማመን ወደ ሸኔ የተቀላቀሉ ወጣቶች የዚህን የጥፋት ቡድን ሴራ በማወቅ ወደ ሕዝቡ መመለሳቸው ጀግንነት መሆኑን ገልጿል የክልሉ መንግሥት።
አሁንም የሸኔ የሽብር ቡድን ድርጊት ውስጥ በመሳተፍ ታሪክ የማይረሳው ስህተት ላለመሥራት የወሰኑ ወጣቶች እጃቸውን በሰላም ለመንግሥት እና ለሕዝቡ እንዲሰጡ ጠይቋል።
ሕዝቡ እያሳየ ያለውን ደማቅ ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርቧል።