የቻይናው ቶዮ ሶላር ኩባንያ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ኢንቨስት ሊያደርግ ነው

ነሐሴ 29/2016 (አዲስ ዋልታ) ቬተናም የሚገኘው ቶዮ ሶላር የተባለው የቻይና ኩባንያ በኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ስር በሚገኙ የኢንቨስትመንት ማዕከላት ኢንቨስት የማድረግ ፍላጎት እንዳለው ገልጿል፡፡

ዋና ስራ አስፈጻሚው ኮርፖሬሽኑ በሚያስተዳድራቸው የኢንዱስትሪ ፓርኮችና የድሬዳዋ ነጻ የንግድ ቀጠና ውስጥ ያሉ የኢንቨስትመንት አማራጮችን፣ መሰረተ ልማቶችን፣ የተለያዩ የኢንቨስመንት ማበረታቻዎችን እንዲሁም በመንግስት በኩል የተደረጉ አጠቃላይ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሪፎርሞች ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በቀጣይም ኩባንያው የቅድመ ኢንቨስትመንት ምልከታውን አጠናቆ ወደ ስራ እንዲገባ አስፈላጊው ድጋፍና ክትትል ይደረጋል ብለዋል፡፡

የቶዮ ሶላር ዋና ስራ አስኪያጅ ሊ ሁያንግ በበኩላቸው ካምፓኒው ወደ ስራ ሲገባም በመጀመሪያው ምዕራፍ 5 ሄክታር የለማ መሬት ተረክቦ ኢንቨስት የማድረግ ፍላጎት እንዳለው ገልጸዋል፡፡

ኩባንያው ወደ ስራ ሲገባም 100 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ኢንቨስት እንደሚያደርግ ገልጸው ከ400 በላይ ለሚሆኑ ዜጎችም በቋሚነት የስራ እድልን ይፈጥራል ብለዋል፡፡

ምርቶቹም መካከለኛው ምስራቅ፣ ህንድና አሜሪካ የምርቶቹ መዳረሻ ገበያዎች ይሆናል ማለታቸውን የኮርፖሬሽኑ መረጃ አመላክቷል፡፡