የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለአፍሪካ ዋንጫ በማለፉ አዲስ አበባ ከተማን ጨምሮ ህዝቡ አደባባይ በመውጣት ደስታውን እየገለጸ ነው

መጋቢት 22/2013 (ዋልታ) – የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለአፍሪካ ዋንጫ በማለፉ አዲስ አበባ ከተማን ጨምሮ ህዝቡ አደባባይ በመውጣት ደስታውን እየገለጸ ነው።
ህዝቡ ብሔራዊ ቡድኑን በማሞገስ የተለያየ ህብረ ዝማሬ በማሰማት ደስታውን እየገለጸ እንደሚገኝ ኢዜአ ዘግቧል።
በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ እየተመራ ለ33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ያለፈው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ኒጀርና ማዳጋስካር ያለምንም ግብ በአቻ ውጤት ጨዋታቸውን በማጠናቀቃቸው ነው።
ቡድኑ ዛሬ ከኮትዲቯር አቻው ጋር ባደረገው ጨዋታ 3 ለ 1 በሆነ ውጤት እየተመራ የመሃል ዳኛው በህመም አቋርጦ በመውጣቱ ጨዋታው እንዲጠናቀቅ ተደርጓል።
ቡድኑ በ9 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ ካሜሩን ለምታስተናግደው 33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ማለፉን አረጋግጧል።
ብሔራዊ ቡድኑ ለአፍሪካ ዋንጫ ሲያልፍ የአሁኑ ለ11ኛ ጊዜ ሲሆን ለመጨረሻ ጊዜ የተሳተፈው እ.አ.አ በ2013 ደቡብ አፍሪካ ባስተናገደችው 29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ መሆኑ ይታወሳል።