የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የማጣርያ ጨዋታዎች ላይ የቀን ለውጥ ተደረገ

ግንቦት 17/2014 (ዋልታ) የኢትዮጵያ ወንዶች ብሔራዊ ቡድን በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ለሚያደርጋቸው ጨዋታዎች የቀን ለውጥ መደረጉን ካፍ አስታውቋል፡፡
በአይቮሪ ኮስት አዘጋጅነት በፈረንጆች 2023 በሚደረገው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ተሳታፊ ለመሆን የሚደረጉ ጨዋታዎች ከቀናት በኋላ መካሄድ የሚጀምሩ ሲሆን “በምድብ መ” ከግብጽ፣ ጊኒ እና ማላዊ ጋር የተደለደለችው ኢትዮጵያ የመጀመሪያ ሁለት ጨዋታዎቿን ከማላዊ እና ግብጽ ብሔራዊ ቡድኖች ጋር ታከናውናለች፡፡
ጨዋታዎቹ ግንቦት 25 እና 29 እንዲደረጉ አስቀድሞ መርኃ ግብር ወጥቶላቸው የነበረ ቢሆንም የቀን ሽግሽግ መደረጉን ካፍ አስታውቋል፡፡
በዚህም ከማላዊ ጋር የሚደረገው ጨዋታ ግንቦት 28 ቀን የሚከናወን ሲሆን ከግብጽ ጋር የሚከናወነው ጨዋታ ደግሞ ሰኔ 2 ቀን 2014 የሚደረግ መሆኑን ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡