የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሴቶች ቡድን ሽንፈት

ጳጉሜ 4/2013 (ዋልታ) በአፍሪካ ሴካፋ ዋንጫ ጠንካራ ተፎካካሪ የነበረው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሴቶች ቡድን በፍጻሜ ጨዋታው 2 ለ1 ተሸነፈ፡፡

በየጨዋታው በርካታ ግቦችን በማስቆጠር ለፍፃሜ ደርሶ የነበረው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቡድን አመሻሽ 10፡00 ያደረገውን የፍፃሜ ጨዋታ  በቪሂጋ 2 ለ 1 ተሸንፎ ውድድሩን አጠናቋል፡፡

ንግድ ባንክ ጭማሪ ሰዓት ላይ በፍፁም ቅጣት ምት በኬንያ አቻው በተቆጠረበት ግብ ነው ተሸንፎ ከአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ ውድድር ውጭ የሆነው፡፡

በ35ኛው ደቂቃ ላይ ጄንትሪክስ ባስቆጠረችው ግብ የኬንያው ቡድን መሪ ቢሆንም በሁለተኛ አጋማሽ ላይ በራሳቸው ግብ ላይ ባስቆጠሩት ግብ ንግድ ባንክ አቻ መሆን ችሎ ነበር፡፡

ጨዋታው 1 ለ 1 በሆነ ውጤት ተጠናቆ በጭማሪ ሰዓት 93ተኛ ደቂቃ ላይ ለቢሂጋ ኩዊንስ በተሰጠ ፍጹም ቅጣት ምት የኬንያው ቡድን አሸንፎ ለአፍሪካ ሻምፒየንስ ሊግ ወደ ግብጽ ማምራት የሚችልበትን እድል ፈጥሯል፡፡

በዞኑ ማጣሪያ ጨዋታ ሎዛ አበራ ኮከብ ግብ አስቆጣሪ ሆና ስታጠናቅቅ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ውድድሩን ሁለተኛ ሆኖ በማጠናቀቁ የ20 ሺ የአሜሪካ ዶላር ተሸላሚ ሆኗል፡፡

ቪሂጋ ደግሞ ምስራቅ አፍሪካን በመወከል በግብፅ ለሚካሄደው የ አፍሪካ ሻምፒዮንስ ተሳታፊ ይሆናል፡፡