የኢትዮጵያ ኤምባሲ በፓሪስ ኦሊምፒክ ለሚሳተፈው ልዑካን ቡድን አቀባበል አደረገ


ሐምሌ 22/2016 (አዲስ ዋልታ) በፈረንሳይ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በፓሪስ ኦሊምፒክ ለመሳተፍ ወደ ስፍራው ላቀናው የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ልኡካን ቡድን አቀባበል አደረገ።

ባሳለፍነው ሀሙስ ማለዳ ወደ ፓሪስ የተጓዘዉ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ልዑካን ቡድን በቆይታው በፈረንሳይ ከሚገኙ ትዉልደ ኢትዮጵያዊያን ጋር በስፖርት ቱሪዝም ዙሪያ መክሯል።

ልኡካን ቡድኑ ዛሬ ደግሞ በፈረንሳይ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ደማቅ አቀባበልና የእራት ግብዣ ተደርጎለታል። ልኡካን ቡድኑ በኤምባሲው ቅጥር የችግኝ ተከላ መርሀ ግብር አከናዉኗል።

በመርሀግብሩ ላይ የተገኙት በፈረንሳይ የኢትዮጵያ አምባሳደርና የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዴኤታ ብርቱካን አያኖ መላዉ ዓለም በጉጉት በሚጠብቀው በኦሊምፒክ ዉድድር ኢትዮጵያ የተሻለ ዉጤት እንድታመጣ ኤምባሲዉ ሁሉንም ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

በእለቱም የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አሸብር ወ/ጊዮርጊስ፣ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ረ/ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉና ሌሎችም ተገኝተዋል።

ከቀጣዩ ሀሙስ ጀምሮ ኢትዮጵያ ለሜዳሊያ የምትጠበቅበት የአትሌቲክስ ዉድድር የሚጀምር ሲሆን በአዉሮፓ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ትዉልደ ኢትዮጵያዊያን በዉድድሩ ስፍራ በመገኘት አትሌቶችን እንዲያበረታቱ ጥሪ ቀርቧል።

ሀብታሙ ገደቤ ከፈረንሳይ ፓሪስ