ጥቅምት 1/2017 (አዲስ ዋልታ) የዜጎችን ደህንነት በተሟላ መልኩ ለማረጋገጥ ለሳይበር ደህንነት ትልቅ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ ገለጹ።
ከዛሬ ጀምሮ ለአንድ ወር “የቁልፍ መሠረተ ልማት ደህንነት ለዲጂታል ሉዓላዊነት” በሚል መሪ ሐሳብ የሚካሄደው የሳይበር ደህንነት ወር በሳይንስ ሙዚየም ተጀምሯል።
በመርኃ ግብሩ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ የኢትዮጵያን ወሳኝ የመሰረተ ልማት አውታሮች ከሳይበር ጥቃት በመጠበቅ ሉዓላዊና ጠንካራ ሀገር ሆና እንድትቀጥል ማድረግ ይገባል ብለዋል።
የሀገር ሉአላዊነትን ለማረጋገጥ የሳይበር ደህንነት ቁልፍና ወቅታዊ ጉዳይ መሆኑን አብራርተው የዲጂታል ሃብቶችን የመጠበቅ እና የዜጎችን ደህንነት በተሟላ መልኩ ለማረጋገጥ ለሳይበር ደህንነት ትልቅ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ነው ያሉት።
በሳይበር ቴክኖሎጂ ልማት የግሉ ዘርፍ የሚጠበቅበትን ሚና እንዲጫወት በማገዝ የወጣቶችን የቴክኖሎጂ ተሰጥኦ ማበልጸግ ይገባል ማለታቸውንም ኢዜአ ዘግቧል።
የሳይበር ደህንነት ወር የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ መርኃ ግብሮችን በማከናወን የሚካሄድ መሆኑም ተጠቁሟል።