የፓን አፍሪካኒዝም አባት
(ቴዎድሮስ ኮሬ)
የፓን አፍሪካኒዝም አባት በመባል የሚታወቀው ኤድዋርድ ዊልሞት ብላይደን ነሐሴ 3፣1832 (እኤአ) በሴንት ቶማስ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ቨርጂን ደሴት፣ ዌስት ኢንዲስ ተወለደ። ብላይደን ወላጆቹ ሮሜዮ እና ጁዲት ብላይደን ከወለዷቸው ሰባት ልጆች ውስጥ ሦስተኛ ልጅ ነበር፡፡ አባቱ ልብስ ሰፊ፤ እናቱ ደግሞ አስተማሪ ነበረች። ቤተሰቡ የሚኖረው የደች ተሐድሶ ቤተክርስቲያንን በሚከታተሉበትና በአብዛኛው አይሁዳዊ እና እንግሊዘኛ ተናጋሪ በሆነ ማህበረሰብ ውስጥ ነበር፡፡
የደሴቶቹ አብዛኞቹ ጥቁሮች በባርነት በነበሩበትና ማንበብና መጻፍ በማይችሉበት ጊዜ የብላይደን ወላጆች ነፃ የነበሩና ማንበብና መጻፍ የሚችሉ ነበሩ። እ.ኤ.አ. በ1842 ቤተሰቡ ብላይደን ብዙ ቋንቋዎችን ወደ ተዋወቀባት ፖርቶ ቤሎ፣ ቬንዙዌላ ተዛወረ። በተጨማሪም ነፃ የወጡ ቬንዙዌላውያን ጥቁሮች በቨርጂን ደሴቶች ውስጥ በባርነት ከተያዙ ጥቁሮች ጋር ተመሳሳይ የሆነ ዝቅተኛ የጉልበት ሥራ ሲሰሩ ተመለከተ።
ቤተሰቡ ወደ ሴንት ቶማስ ሲመለሱ፣ ብላይደን የደች ተሐድሶ ቤተክርስቲያን ፓስተር ሬቭር ጆን ፒ. ኖክስ ተማሪ ሆነ። ቄስ ኖክስ በብላይደን ምሁራዊ ችሎታ ይደነቁ ነበር፡፡ ብላይደን በቄስ ኖክስ አማካይነት ቄስ ለመሆን ወሰነ። በሜይ 1850 ብላይደን ከቄሱ ሚስት ወይዘሮ ኖክስ ጋር በመሆን ኒው ጀርሲ ሩትገርስ ቲዎሎጂካል ኮሌጅ ለመመዝገብ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ሄዶ ነበር፤ ነገር ግን በጥቁርነቱ የተነሳ ተቀባይነት አላገኘም።
ብላይደን ትኩረቱን ወደ አፍሪካ አዞረ። የምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር ላይቤሪያ በ1847 ነፃ ሀገር ነበረች። በ1850 ብላይደን ላይቤሪያ ሄዶ እንዲያስተምር የቀረበለትን ጥያቄ ተቀበለ። በጥር 1851 ወደ ላይቤሪያ ሄደ፤ ብዙም ሳይቆይ በሞንሮቪያ አሌክሳንደር ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተቀጠረ። እዚያም በሥነ-መለኮት፣ በጥንታዊ ታሪክ፣ በጂኦግራፊ እና በሂሳብ ላይ ጥናት ማድረግ ጀመረ። በ1858 ብላይደን የፕሬስባይቴሪያን ሚኒስትርነትን በማግኘት የአሌክሳንደር ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ሆነ። በላይቤሪያው ፕሬዚዳንት ጆሴፍ ሮበርትስ አማካኝነት የወቅቱ የሀገሪቱ ብቸኛ ጋዜጣ የነበረው የላይቤሪያ ሄራልድ ጋዜጣ አዘጋጅ ሆኖ ተሾመ።
ብላይደን በወቅቱ በአውሮፓ እና በሰሜን አሜሪካ በእጅጉ ተስፋፍቶ የነበረውን ጥቁሮችን ዝቅተኛ አድርጎ የመቁጠር አመለካከትንና ተግባርን ተቃውሞ ተከራክሯል። ብዙም የማይታወቁ፤ ነገር ግን የአፍሪካ የዘር ግንድ ያላቸውን ስኬታማ ሰዎች ምሳሌዎች አድርጎ በመጠቀም ለጥቁሮች እኩልነት ተሟግቷል። በ1856 እና 1887 መካከል ብላይደን በርካታ መጽሃፎችን እና በርካታ መጣጥፎችን ጽፏል፡፡ ከመጽሐፎቹም መካከል “ድምፅ ከምትደማው አፍሪካ” (1856)፣ “የአፍሪካ ዘር መገለጥ”፣ “አፍሪካ ለአፍሪካውያን” (1872) እና “ክርስትና፣ እስልምና እና የጥቁር ዘር” (1887) ተጠቃሽ ናቸው።
ብላይደን ህዳር 16 ቀን 1875 ኢትዮጵያ በቅኝ ገዥ አረቦች የምትመራውን ግብፅን በጉንደት ጦርነት ድል ስለማድረጓ በይፋ ተናግሯል። ብላይደን እና ማርቲን ሮቢንሰን ዴላኒ የጉንደትን ድል የአፍሪካ ድል ነው ሲሉ አድንቀዋል።
ብላይደን የፖለቲካ ስልጣኑን በብቸኝነት ለመቆጣጠር ይቋምጡ የነበሩትን የላይቤሪያ ጥቁር እና ሙላቶ ልሂቃንን ሞግቷል። በ1860ዎቹ እና በ1870ዎቹ መጀመሪያ ላይ ብላይደን የላይቤሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የላይቤሪያ ኮሌጅ የክላሲክስ ፕሮፌሰር መሆን ችሎ ነበር። እውቀት ያላቸውና ባለሙያ የሆኑ ጥቁር ምዕራብ ህንዶችን እና አፍሪካ አሜሪካውያንን ወደ ላይቤሪያ ጠራ። ይህ ተግባሩም ከላይቤሪያ ልሂቃን ከባድ ተቃውሞ አስከትሎበት ነበር። ቢሆንም በ1885 ብላይደን ለላይቤሪያ ፕሬዚዳንትነት ተወዳድሯል። በውድድሩም ከተሸነፈ በኋላ ወደ ጎረቤት ሴራሊዮን ተሰደደ። ኤድዋርድ ዊልሞት ብላይደን በሴራሊዮን የካቲት 7 ቀን 1912 ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ።